ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ለአዳዲሶቹ የሱዳን መሪዎች የመልካም ምኞት መግለጫ አስተላለፉ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለአዳዲሶቹ የሱዳን መሪዎች የመልካም ምኞት መግለጫ አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በዛሬው እለት ባስተላለፉት መልእክት፥ ጀነራል አብዱል ፈታህ ቡርሀን 11 አባላት ያሉት ሉዓላዊ ምክር ቤት መሪ ሆነው በመመረጣቸው እንኳን ደስ አለዎት ብለዋል።

እንዲሁም የነሐሴ 11 የሽግግር መንግስት ስምምነት ፊርማን ተከትሎ ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው ለተመረጡት አብደላ ሀምዶክ የመልካም ምኞት መግለጫ ማስተላለፋቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

ጄኔራል አብድል ፈታ ቡርሃን አዲስ የተቋቋመው እና 11 አባላት ያሉት የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት መሪ ሆነው በትናንትናው እለት ነው የተመረጡት።

11 አባላት ያሉት የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ሸንጎ ኦማር ሀሰን አል በሽር ከስልጣን ከወረዱበት ሚያዚያ 2019 ጀምሮ ሀገሪቱን ሲመራ የቆየውን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤትን ተክቶ ትናንት ነው በይፋ ስራውን የጀመረው።

ሌተናል ጄነራል አብደል ፈታህ አብደልራህማን ቡርሃን አዲስ የተቋቋመው የሱዳን ሉአላዊ ምክር ቤት መሪ በመሆን በትናንትናው እለት ቃለ መሃላ ፈጽመዋል።

ጀኔራል ቡርሃን ከሶስት ዓመት በላይ የሽግግር ጊዜ ውስጥ የሉዓላዊ ሸንጎውን ለ21 ወራት በበላይነት የሚመሩት ሲሆን፥ የሲቪል ተወካዮች ደግሞ ቀጣዮቹን 18 ወራትን ይመራሉ።

11 አባላት ያሉት ሉዓላዊ ምክር ቤት በትናንትናው እለት በይፋ ስራውን መጀመሩን ተከትሎም አብደላ ሀምዶክ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን በትናንትናው እለት ቃለመሃላ ፈፅመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚነታቸውን የለቀቁት ባለፈው ዓመት ነበር።

አብደላ ሃምዶክ በኢኮኖሚ ተንታኝነት ከ30 ዓመት በላይ ልምድ ያላቸው ሲሆን፥ ከካርቱም ዩንቨርሲቲና ከታወቁ የእንግሊዝ ትምህርት ተቋሞት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።

ወታደራዊ ምክር ቤቱና የነጻነትና የለውጥ ኃይሎች ጥምረት የአገሪቱን የሽግግር መንግሥት ለመጀመር ባለፈው ቅዳሜ መፈራረማቸው የሚታወስ ነው።

(ምንጭ፦ ኤፍቢሲ)