ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እንዲመጣ የምታደርገው ጥረት ተጨባጭ ለውጥ እያሳየ መሆኑ ተገለጸ

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እንዲመጣ የምታደርገው ጥረት ተጨባጭ ለውጥ እያሳየ መሆኑ ተገለጸ።

ከ7ኛው ቶኪዮ ለአፍሪካ ልማት ጎን ለጎን በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ትኩረቱን አድርጎ እየተካሄደ ባለው ውይይት ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ፤ ኢትዮጵያ በአካባቢው ሰላምና ብልፅግና  እንዲሰፍን ቁርጠኛ ተግባር እያሳየች መሆኑን ገልጸዋል።

አካባቢው በርካታ ቁጥር ያለው ወጣት መገኛ መሆኑን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠር የመሪዎች የቀጣይ ተግባር ሊሆን ይገባል ብለዋል። በአካባቢው ዘላቂ ሰላምና የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲመጣ በመደመር እሳቤ ልንሰራ ይገባልም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢትዮጵያ በቀጠናው ሰላም እንዲሰፍን በተግባር እያሳየች ያለው ሚና የሚደነቅ መሆኑን በመጥቀስ፤  በቅርቡ በሱዳን የተደረሰው ስምምነት የኢትዮጵያን ሚና በአብነት አንስተዋል።

የአካባቢውን ሰላም እና ልማት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የጃፓን ድጋፍ እንደማይለይም አረጋግጠዋል። የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሙሀመድ አብዱላሂ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በአካባቢው አንድነት እና ሰላም እንዲመጣ በሚደረገው ጥረት ሚናዋ ልቆ ይታያል ነው ያሉት።