ጠ/ሚ ዶ/ር ዐብይ አህመድ እስራኤልን ሊጎበኙ ነው

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ በመጪው እሁድ እስራኤልን ይጎበኛሉ፡፡

የእስራኤል ኤምባሲ እንዳስታወቀው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከእስራኤል አቻቸው ቤንያሚን ኔትኒያሁ በቀረበላቸው ግብዣ መሰረት ነው ሀገሪቱን የሚጎበኙት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ በቆይታቸው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔትኒያሁን ጨምሮ ፕሬዚዳንት ሪውቨን ሪቭሊኒን ጋር እንደሚወያዩ ተገልጿል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ጉብኝት በኢትዮጵያና እስራኤል መካከል ለረጅም ጊዜ የቆየውን ሁለንተናዊ ግንኙነት እንደሚጠናክረውኢምባሲው ለዋልታ ቴልቭዥን በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ እንደ ያድ ቫሼም ያሉትን ታሪካዊ ሃውልቶችን ጨምሮ  የእስራኤል ብሄራዊ የሳበር መከላከያ ተቋምን ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ያድ ቫሼም በናዚ በግፍ የተጨፈጨፉ አይሁዶች መታሰቢያ ሃውልት ሲሆን፤ በየዓመቱ በመቶ ሺህዎች የሚጎበኝ ታሪካዊ መካነ መቃብር ስፍራ ነው፡፡

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ጉብኝት የአፍሪካ እና እስራኤል ትብብርን የሚያጠናክር፣ እስራኤልም ፊቷን ወደ አፍሪካ ማዞሯን የሚያመላክት እንደሆነ መግለጫው ጠቅሷል፡፡