ኢትዮጵያና ኬንያ በድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ላይ በጋራ ለመስራት ስምምነት ተፈራረሙ

ኢትዮጵያና ኬንያ በድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ላይ በጋራ ለመስራት ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አቶ ብርሀኑ ጸጋዬ የኬንያውን ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ተቋም ልዑካን ቡድን በዛሬው ዕለት በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ በንግግራቸው ኢትዮጵያና ኬንያ የረጅም ጊዜ ግንኙነት ያላቸው አገራት በመሆናቸው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በጋራ ሲሰሩ መቆየታቸውንና፤ እየሰሩ መሆናቸውንም ተናግረው ግንኙነታቸው ለሌሎች አፍሪካ አገራት ምሳሌ መሆን የሚችል ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

አክለውም ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ከኬንያው አቻቸው ጋር በድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ላይ በጋራ ለመስራት መነጋገራቸውን አውስተው፤ ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና በድንበር ተሸጋሪ ወንጀሎች ዜጓቿን ለከፋ አደጋ እየተጋለጡ በመሆኑ፤ በዚህም በኬንያና በኢትዮጵያ ድንበር በኩል አቋርጠው ወደ ደበብ አፍሪካና፣ ታንዛኒያና እንዲሁም ወደ ሌሎች አገሮች ለመሔድ ሲሉ ለጉዳት እየተዳረጉ በመሆኑ በትኩረት በጋራ ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ሽብርተኝነትን፣ ሙስናን በሙስና ምክንያት ሀብት የማሸሽ ወንጀሎችን በጋራ በተጠናከረ መልኩ መከላከል እንደሚያስፈልግ እና የኬንያ መንግስትም በዚህ ረገድ ያለውን ልምድ እና እወቀት በማጋራት በኩል የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት እንዲሁም በአቅም ግንባታና በቴክኒካል ድጋፍ በኩልም እገዛ እንድታደርግ ጠይቀዋል፡፡

የኬንያው አቃቤ ህግ ጽ/ቤት ዳይሬክተር ኑረዲን መሀመድ ሃጂ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገራት በታሪኳ የተለየች አገር መሆኗን ተናግረው፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና ፖለቲካው ዘርፍም እያደረገች ያለውን ለውጥ አድንቀዋል፡፡

በተለይም ኢትዮጵያ በሙስና ላይ ያላት ቁርጠኛ አቋምና እየወሰደች ያለውን እርምጃ አድንቀው፣ አገራቸው ኬንያም እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ በዚህ ረገድ ጠንካራ አቋም በመያዝ ለለውጥ ለመስራት ዝግጁ መሆኗን ጠቅሰው፤ ሁለቱም አገራት ያላቸውን የጋራ ወዳጅነት ለማጠናከርና ለማስቀጠል እንዲሁም ለአገራቱ ደህንነት ሲባል በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና በድንበር ተሸጋሪ ወንጀሎች ላይ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ለመፈራረም መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡

ሀገራቱ የተለያዩ ልምዶችን እየተለዋወጡ በአቅም ግንባታና በቴክኒክ ድጋፍም እየተረዳዱ እንደሚሰሩ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ ዐቃቤ ሕግ ማህበር አባል እንዲትሆን ጥሪ አቅርቧል፡፡

በመጨረሻም ኢትዮጵያ በጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ በአቶ ብርሀኑ ጸጋዬ እንዲሁም ኬንያ ፤ በኬንያ አቃቤ ህግ ጽ/ቤት ዳይሬክተር ኑረዲን መሀመድ ሃጂ በኩል የስምምነት ሰነዱን ተፈራርመዋል፡፡ (ምንጭ:-ጠቅላይ አቃቤ ሕግ)