ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና የእስራኤሉ አቻቸው ቤኒያሚን ኔታኒያሁ በሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ዙሪያ በጋራ ማብራሪያ ሰጡ

ለይፋዊ የስራ ጉብኝት እስራኤል የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና የእስራኤሉ አቻቸው ቤኒያሚን ኔታኒያሁ በዛሬው ዕለት በጋራ በሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ዙሪያ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ኢትዮጵያ እየወሰደቻቸው ያለውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎች ያደነቁ ሲሆን፤ እስራኤላውያን ባለሃብቶች በንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሳተፉ እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

እስራኤል በኢትዮጵያ በተለይም በጸጥታ፣ በቴክኖሎጂ፣ በግብርናና አይሲቲ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እንደምትሰራ ያረጋገጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኔሁ፤ ለኢትዮጵያኖች ያላቸውን የመልካም አዲስ ዓመት ምኞትም አስተላልፈዋል።

ሁለቱ አገራት ማሻቭ በተሰኘው ድርጅት አማካይነት ሲያደርጉት የነበረውን ትብብርም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በበኩላቸው፤ በንግስት ሳባና ንጉስ ሰለሞን አማካይነት ግንኙነት የጀመሩት ኢትዮጵያና እስራኤል፤ የቆየ የታሪክ፣ የባህልና የሃይማኖት ትስስር እንዳላቸው አስታውሰዋል፡፡

ትውልደ ኢትዮጵያ ቤተ እስራኤላውያንም በሁለቱ አገራት መካከል እንደ ድልድይ ሆነው ለግንኙነቱ መጠናከር የበኩላቸውን አስተዋፅዖ እንደሚያበረክቱ ያላቸውን እምነትም ገልፀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ በደረሰው አደጋ ሕይወታቸውን ባጡት ሦስት እስራኤላውያን ሕልፈተ-ሕይወት የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን የገለጹ ሲሆን፤ የእስራኤል ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በቴሌኮም፣ በአቬሽንና ሎሎችም ዘርፎች  እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በቅርቡ በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ላይ ቃጠሎ በደረሰበት ወቅት እስራኤላውያን ባለሙያዎች በቦታው በመገኘት እሳቱን ለማጥፋት ላደረጉት ትብብርም አመስግነዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ እና ልኡካቸው በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ፅህፈት ቤት የክብር አቀባበል ተደርጎላቸዋል።