የኢትዮጵያ የሰላም አስከባሪ ኃይል በሶማሊያ ላበረከተው ሚና አሚሶም ምስጋና አቀረበ

በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት ተልዕኮ ስር ለተሰማራው የኢትዮጵያ የሰላም አስከባሪ ኃይል ላበረከተው ሚና አሚሶም ምስጋና አቀረበ፡፡

ላለፈው አንድ ዓመት ኃላፊነቱን በአሚሶም ጥላ ሰር ተወጥቷል የተባለው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል የሶማሊያ ሰላም እንዲሻሻል ጉልህ ሚና በመጫወቱ ምስጋና እንደሚገባው የአሚሶም ኃይል ዋና አዛዥ ሌቴናል ጀነራል ይልማ ጥጋቡ አስታውቀዋል፡፡

በተለይም ሰላም አስከባሪው ላለፈው አንድ ዓመት ከሶማሊያ የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት የሽብር ኃይሎችን ተጠራርገው እንዲወጡ በማድረግ የአገሪቱን የሽግግር እቅድ እንዲሳካ ሙያዊ ኃላፊነታቸውንና ብቃታቸውን በአግባቡ ተወጥተዋል ብለዋል፡፡

የሰላም አስከባሪ ኃይሉ የአንድ ዓመት ተልዕኮውን በማጠናቀቁ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በአሚሶም ዋና ማዘዣ በበለደወይን ከተማ የእውቅና ምስጋና መርሃ ግብሩ እንደተዘጋጀላቸው አሚሶም በትዊተር ገፁ አስታውቋል፡፡

በአሚሶም ጥላ ስር ሶማሊያን ከገባችበት የፀጥታ ችግር እንድትወጣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ20 ሺህ በላይ የሰላም አስከባሪ ወታደሮች በሰላም ማስከበር ስራ ላይ ተሰማርተው በማገልገል ላይ ነበሩ፡፡