በደቡብ ክልል የሰፈነውን ሰላም ለማስጠበቅ ህብረተሰቡ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ

በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል አሁኑ ወቅት የሰፈነውን አንጻራዊ ሰላም ለማስጠበቅ የህብረተሰቡ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳው ጥሪ አቀረቡ።

አቶ ርስቱ ይርዳው የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ እንዳሉት፣ የክልሉ ህብረተሰብ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በመሆን ባበረከቱት አስተዋጽኦ የአካባቢው ሰላም ወደ ቀድሞው ሁኔታ እየተመለሰ ነው።

ሰላሙ ዘላቂ እንዲሆን ህዝቡ የአካባቢውን ደህንነት መከታተል በተለይ ወጣቶች ለክልሉ ደህንነት ከመንግስት ጎን በጽናት ሊቆሙ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የደቡብ ክልል እንደሚታወቀው አቃፊ ህብረ ብሄራዊና ዛሬ በክልሉ ለተገኙ ድሎች አብሮ የሰራ እንደመሆኑ የሀገር ሽማግሌዎች የኃይማኖት አባቶች ሰላምን በማስጠበቅ የህዝቦችን አንድነትና አብሮነት ለማጠናከር መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

በክልሉ በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ለወጣቱ የስራ ዕድል በተገቢው መንገድ መፍጠር እንዳልተቻለ ጠቁመው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴውና የአገልግሎት ዘርፉ በተለይ ቱሪዝም የተዳከመ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህንን ወደነበረበት ለመመለስና የህዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንዲቻል በትብብር መስራት ያስፈልጋል።

አቶ ርስቱ እንዳመለከቱት ፍትህን ለማስፈንና የኑሮ ውድነትን ለማስተካከል የሚቻለው ሰላም ሲኖር በመሆኑ ለዚህም ቅድሚያ መስጠትና ትልቅ ዋጋ መስጠት ይገባል።

በአዲሱ ዓመት በመንግስት በኩል የነበሩ የአሰራር ክፍተቶችና ከአደረጃጀት ጋር በየአካባቢው የሚነሱ ቅሬታዎች በአግባቡ በመፈተሽ ምላሽ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።

“ ለሁሉም የክልሉ ህዝብ በፍትሀዊነት ህግን የማስከበር ስራ እንዲሰራ ይደረጋል “ብለዋል።

“በዚህ ተግባር ምሁራንን ፣ ወጣቶችና ሴቶችን ጨምሮ ሁሉም የክልሉ ህብረተሰብን ከጎናችን አድርገን እንሰራለንም “ብለዋል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ እንደገለጹት አዲሱ ዓመት በግብርናው መስክ ለገበሬው ልዩ ድጋፍና የቴክኖሎጂ አቅርቦት በማድረግ ባለፉት ዘመናት በጸጥታ ችግር ምክንያት የታጣውን ለማካካስ የሚሰራበት ይሆናል።

በተያዘው የመኽር ወቅት ቀሪ ጊዜያት ምርታማነትን መጨመር በሚያስችሉ ስራዎች ላይ ርብርብ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

በ2012 ዓ.ም ባለፉት ዓመታት በሀገሪቱ ብሎም በክልሉ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉበት እንደሚሆነም አመልክተዋል።

“ ወደኋላ የሚጎትቱ በተለይ አንድነታችንን እና አብሮነታችንን የሚሸረሽሩ አስተሳቦችን ለማስወገድ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ክልል የሰፈነው አንጻራዊ ሰላም ለማስጠበቅ ህብረተሰቡ እንቀድሞው ሁሉ በአዲሱ ዓመትም ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጠል ጥሪ አቅርበዋል።

በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የክልሉ ህዝቦች ስጋት ላይ የወደቁበት ሁኔታ እንደነበር አስታውሰው መጪው ዘመን የህዝብ ጥያቄዎችና ፍላጎቶች በሰከነና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ምላሽ እንዲያገኙ መንግስት ጥረት እንደሚያደርግ አመልክተዋል።

አዲሱ ዓመት የሰላም የፍቅር የአንድነትና አብሮነት እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

(ምንጭ፡-ኢዜአ)