በአዲሱ ዓመት ለሰላም እና ለኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል- አቶ ተመስገን ጥሩነህ

በአዲሱ ዓመት ለሰላም እና ለኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራባቸው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ አስታወቁ፡፡

በአመቱ ለሰላም፣ ለቱሪዝም፣ ለኢንቨስትመንት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ እና ለግብርና ዘርፎች ትኩረት ይደረጋል ነው ያሉት፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ለመላው የአማራ ህዝቦች፣ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን መልካም አዲስ ዓመትን ተመኝተዋል፡፡

አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መረጃ ባለፈው ዓመት የአማራ ክልል ሠላም አሳሳቢ ሁኔታ ላይ የደረሰበት፣ በርካታ ዋጋ የተከፈለበት ወቅት እንደነበር፣ ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ ግን አንፃራዊ የሰላም ሁኔታ መታየቱን ተናግረዋል፡፡

በ2012 የሥራ ዘመን ለሰላም፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለኢንቨስትመንት እና ለቱሪዝም ዘርፎች ልዩ ትኩረት በመስጠት እንደሚሠሩ አቶ ተመስገን አስታውቀዋል፡፡

ሰላም ለማኅበራዊ፣ ለፖለቲካዊ እና ለሁለንተናዊ ልማቶች ቁልፍ በር በመሆኑ ከየትኛው ጊዜ በላይ ሕግ የማስከበር ሥራውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የገለጹት አቶ ተመስገን፤ ኅብረተሰቡም ጥያቄዎቹ እንዲመለሱ ሰላም የማስከበር ሥራው ላይ ተባባሪ እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡

በሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ ክልሉ በ2012 የሥራ ዘመን በገጠር እና በከተማ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ እየሠሩ መሆናቸውንም ነው የገለጹት፡፡

በኢንቨስትመንት ዘርፍ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ ትኩረት አድርገው እንደሚሠሩ፣ በተለይም የሀገር ውስጥ የዘይት ፍላጎትን የሚሸፍነው በክልሉ ውስጥ እየተገነባ ያለው የዘይት ፋብሪካ ሥራ እንደሚጀምር ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል የቱሪዝም ዘርፉ እስካሁን ያልተሠራበት፤ ነገር ግን የተሻለ ገቢ የሚገኝበት እንደነበር ገልጸው፣ ሰላምን እና ቱሪዝምን በማስተሳሰር ቅርሶችን በመጠገን፣ ባሕልን በማስተዋወቅ እና መዳረሻዎችን በማስፋፋት ገቢን ለመጨመር ትኩረት እንደሚደረግ አቶ ተመስገን ተናግረዋል፡፡ መረጃው የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ነው፡፡