አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የኖርዌይ የውጭ እና የመከላከያ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር ተወያዩ

የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ዛሬ መስከረም 5 ቀን 2011 ዓም የኖርዌይ የውጭ ጉዳይ እና የመከላከያ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አኒከን ሁይትፈልድት እና ልኡካቸውን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ሁለቱ ወገኖች በሁለትዮሽ፣ በቀጠናዊ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ውይይት አድርገዋል።

ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት አንደገለጹት ኢትዮጵያ እና ኖርዌይ ረጅም ዘመናትን የስቆጠረ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸው፤ ግንኙነቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እየተሰራ ነው ብለዋል።

በኖርዌይ የልማት ትብብር አማካኝነት ኖርዌይ በኢትዮጵያ በማህበራዊና በኢኮኖሚው ዘርፍ እያደረገች ያለውን ጉልህ እንቅስቃሴ በተመለከተ አቶ ገዱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን አጠቃላይ ሪፎርም በተመለከተ ገለጻ በማድረግ ኖርዌ ለሪፎርሙ መሳካት ድጋፏን አጠናክራ እንድትቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ እና በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍንና ኢኮኖሚያዊ ውህደት እንዲመሰረት እየተጫወተች ያለውን ሚና በተመለከተም ሚኒስትሩ ሰፊ ገለጻ አድርገዋል። ኢትዮጵያ እና ኖርዌይ በዓለም አቀፍ መድረኮች በአየር ንብረት ለውጥ እና ተያያዥ ጉዳዮች ጠንካራ ግንኙነት እንደላቸውና በትብብር እየሰሩ መሆኑንም ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

የኖርዌይ የውጭ ጉዳይ እና የመከላከያ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አኒከን ሁይትፈልድት በበኩላቸው በኢትዮጵያ እተካሄደ ያለውን አጠቃላይ ሪፎርም ኖርዌ እንደምታደንቅ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለሴቶች እኩልነት በሰጠችው ትኩረት በርካታ ሴቶች ተጠቃሚ መሆናቸውን እንደተገነዘቡም ገልጸዋል። በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ለቀጠናው ሰላምና መረጋጋት ገልህ ሚና እንደሚጫወት እምነታቸው መሆኑንም አብራርተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ በቀጠናው እየተጫወተች ያለውን አጠቃላይ እንቅስቃሴም አድንቀዋል። ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮችም ጉልህ ሚና የምትጫወት አገር መሆኗን በማንሳት በዚህ በኩል ከኖርዌይ ጋር ያላትን ግንኙነት አጠናክራ እንድምትቀጥል እምነታቸው መሆኑንም አኒከን ሁይትፈልድት በንግግርቸው አንስተዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖንን ለመቋቋም ኢትዮጵያ በደን ተከላ እያደረገች ያለውን ከፍተኛ አንቅስቃሴም አድንቀዋል።

በኢትዮጵያ ጉብኝት በማደረግ ላይ የሚገኙው የኖርዌይ የውጭ ጉዳይ እና የመከላከያ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በኖርዌይ ፓርላማ ውስጥ መቀመጫ ካላቸው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተወከሉ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፓርላማ የውጭ እና የመከላከያ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር በመወየት የልምድ ልውውጥ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ እና ኖርዌይ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የመሰረቱት በ1939 ዓም ሲሆን፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ ስቶክሆልም በሚገኘው ኤምባሲዋ በኩል ከኖርዌይ ጋር ያላትን ግንኙነት አጠናክራ በመቀጠል ላይ ትገኛለች።

በተመሰሰይ ኖርዌይ በ1984 ዓም በአዲስ አበባ ኤምባሲዋን በመክፈት ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግኑኝነት አጠናክራ በማስቀጠል ላይ እንደሚትገኝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።