ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ያሳተፈ፣ የፌዴራሊዝም ሥርዓትን የሚያጠናክር ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ እንዲደረግ ተጠየቀ

የአማራ ምሁራን መማክርት ጉባኤ ስብሰባ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል።

ለሁለት ቀናት በባሕር ዳር ከተማ ሲካሄድ የቆየው የአማራ ምሁራን መማክርት ጉባኤ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ መክሯል፡፡

የመማክርት ጉባኤው በዋናነት የአማራ ሕዝብ በሚያነሳቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ በስፋት ሲመክር ቆይቷል፡፡ ዛሬ ጉባኤው ሲጠናቀቅም ባለዘጠኝ ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቷል።

በዚህ የአቋም መግለጫ ከተካተቱ ሀሳቦች መካከልም ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ያሳተፈ፣ የፌዴራሊዝም ሥርዓትን የሚያጠናክር ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ እንዲደረግ የሚጠይቀው ይገኝበታል።

የሕዝቦችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ፣ ሁሉም ቋንቋዎችና ባሕሎች እንዲበለፅጉ በሚያግዝ መልኩም ማሻሻያው እንዲከናወንም ነው የመማክርት ጉባኤው የጠየቀው፡፡

ዲሞክራሲ፣ ፍትህ እኩልነትና ነፃነት እንዲሁም ብልፅግና የሰፈነባት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግም ከሌሎች ወንድምና እህት ኢትዮጵያውያን ጋር ይበልጥ ተባብሮ ለመስራት መወሰኑንም በመግለጫው አንስቷል፡፡

የህዝቡ ፈታኝ ችግር የሆኑትን የስራ አጥነትና የኑሮ ውድነትን ለመቀነስም የክልሉንና የመላ ኢትዮጵያውያንን እምቅ አቅምና ክህሎት በመጠቀም ይሰራል ነው ያለው፡፡

የክልሉን ተፈጥሯዊ፣ ባህላዊ፣ ቁሳዊ፣ መንፈሳዊ ፀጋዎችንና ሀገር በቀል እውቀቶችን በመጠቀምና በቴክኖሎጂ በማገዝ ለህዝብ ጥቅም ለማዋል በትኩረት እንደሚሰራ አንስቷል፡፡

ቀደምት አባቶች በሀገር መንግስት ግንባታ ሂደት የነበራቸውን ጉልህ ሚናና ውለታ በፅንፈኛ ትርክት ያልተገባ ትርጉም መስጠት አማራ ጠልነት እንዲስፋፋ በሴራና በተደራጀ ሁኔታ ሲሰራበት ቆይቷል ያለው መግለጫው፤ ይህ ለሀገራዊ ህብረት አደጋ በመሆኑ እንዲቆምና እንዳይቀጥል ይሰራል ብሏል፡፡

ሰሜኑን ከደቡብ ምስራቁን ከምዕራብ ያገናኘው፣ የኢትዮጵያ እውቀትና ጥበብ ከዘመን ዘመን የተሻገረበትና ትውልድ የተጋመደበትን የአማርኛ ቋንቋ በማጥላላት እየተደረገ ያለውን ዘመቻ አውግዟል የአቋም መግለጫው፡፡

አብሮነት የሚዳብረውና ብልፅግና የሚረጋገጠው ሁሉም ኢትዮጵያዊ በነጻነት በፈለገው ስፍራ የመኖርና የመስራት መብቱ ሲጠበቅለትና ሀብት የማፍራት መብቱ ሲረጋገጥለት እና ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎቹ ሲመለሱለት መሆኑን አንስቷል፡፡

የአማራ ህዝብ የእኩልነት፣ የፍትህ፣ የዴሞክራሲና የነፃነት ትግል ግብ እንዲመታ በየትኛውም ስፍራ የሚገኝ የአማራ ህዝብ የፖለቲካ፣ የሃይማኖትና ሌሎች የአመለካከት ልዩነቶች ሳይበግሩት በአንድነት እንዲቆምም ነው ጥሪ ያቀረበው፡፡