የሽብር ጥቃት ለመፈጸም በዝግጅት ላይ የነበሩ የአልሸባብና የአይ ኤስ የሽብር ቡድን አባላት በቁጥጥር ስር ዋሉ

በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ዝግጅት የነበራቸው የአልሸባብና የአይ ኤስ የሽብር ቡድን አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለፀ።

ጉዳዩን አስመልክቶ የብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት የሰጠው መግለጫ ሙሉ ቃል ይህን ይመስላል።

በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ዝግጅት የነበራቸውየአልሸባብ እና የአይ ኤስ የሽብር ቡድን አባላት በቁጥጥር ስር ውለዋል።

አልሸባብ እና አይ ኤስ የሽብር ቡድኖቻቸውን ወደ አዲስ አበባ እና የተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በመላክ በኢትዮጵያ የሽብር ጥቃት በመፈፀም በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳይ ለማድረስ እንዲሁም የሀገራችንን በጎ ገፅታ ለማበላሸት በዝግጅት ላይ እንዳሉ የብሄራዊ የመረጃ ደህንነት አገልግሎት ባደረገው ጥብቅና የተቀናጀ ክትትል ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ይህንን የጥፋት ተግባር ለመፈፀም ሀገር ውስጥ የገባው አንድኛው የአልሸባብ የሽብር ቡድን በሙሐመድ አብዱላሂ ዱለት በሀሰተኛ ስሙ ያህያ አሊ ሃሰን የሚመራ ሲሆን፤ የሽብር ጥቃት ተልዕኮ ይዞ በጅቡቲ በኩል ወደ አዲስ አበባ ከተማ በመግባት ህዝብ የሚባዛባቸውን ቦታዎች እንዲሁም የሀይማኖት ክብረ በዓል የሚካሄድባቸውንና የተለያዩ ሆቴሎችን የመለየትና የፎቶግራፍ መረጃዎችን የመሰብሰብ ጥናት በማድረግ ወደ ሽብር ተግባር ለመግባት በዝግጅት ላይ እንዳለ በብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ከጅቡቲ ወደ ሀገራችን ሲገባ ጀምሮ ክትትል ሲደረግበት ስለነበር በአዲስ አበባ ቦሌ አካባቢ በቁጥጥር ስር ውሏል።

ከእርሱ ጋር በመሆን የተለያዩ ጥናቶችን ሲያካሄዱ የነበሩና ጁቡቲ የሚገኙ አብደክ መሃመድ ሁሴንና ሬድዋን መሃመድ ሁሴን የተባሉት ግብረ አበሮቹም ጅቡቲ ከሚገኘውና ሁኔታውን ሲያመቻችላቸው ከነበረው ሌላ የአልሸባብ አባል በቅፅል ስሙ ስመተር መሀመድ ኢማን ዩሱፍ የተባለውን ጨምሮ ከሀገሪቱ የመረጃ ተቋም ጋር በመቀናጀት በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል።

አልሸባብ የሽብር ጥቃት እንዲፈፅሙ ካሰማራቸው ሌሎች ቡድኖች ውስጥም ከደቡባዊ ሶማሊያ ተነስተው ሱማሊላንድ ሐርጌሳ ከተማ ከገቡ በኋላ ወደ ሀገር ውስጥ ለመግባት ዝግጅት ሲያደርጉ ከነበሩ ሌሎች የሽብር ቡድኑ አባላት መካከልም ይሳቅ አሊ አደንና አደን ሙሃሙድ መሃመድ በቅፅል ስሙ አደን ቦራይ የተባሉት የፈንጅና የአጥፍቶ መጥፋት ስልጠና የወሰዱና የቡድኑ ቁልፍ አባላት ከመነሻቸው ጀምሮ በተደረገባቸው ክትትል ከሱማሊላንድ የመረጃ ተቋም ጋር በመቀናጀት በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ሶማሊላንድ በቁጥጥር ስር ከዋሉት ሌሎች የአልሸባብ ሽብር ቡድን አባላት መካከል ኢሳቅ አሊ አደን የተባለው የሽብር እቅዱን ለመፈፀም እንዲያመቸው ከሶማሊያ ክልል ቦህ ወረዳ ጨርቃን ቀበሌ ኢብራሂም ዓሊ አደን በሚል ሃሰተኛ የነዋሪነት መታወቂያ በእጁ ይዞ የተገኘ ሲሆን አደን ማሕሙድ መሐመድ ወይም አደን ቦራይ የተባለው በበኩሉ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁለት የሂሳብ አካውንት በመክፈት ለሽበር ተልዕኮ መፈፀሚያ ሊጠቀሙበት የነበረ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ በተደረገው ጥብቅ ክትትል መገኘቱን ለማረጋገጥ ተችሏል።

ከእነዚህ በተጨማሪም ተመሳሳይ ተልእኮ ይዞው ወደ ሃገር ውስጥ ከገቡት መካከል ዒድ መሃመድ ዓሊ የተባለው በሶማሊ ክልል ጨርጨር ዞን አራርሶ ወረዳ፣ በሽር ዑስማን አብዲ በዚሁ ክልል ፊቅ አከባቢ እንዲሁም ዑስማን አሊ ሁሴን የተባለው በኦሮሚያ ክልል በሞያሌ ከተማ በቁጥጥር ስር ውሏል።

በተያያዘ በኢትዮጵያ ላይ በተደጋጋሚ የሽብር ጥቃት እንደሚፈጽም ሲዝት የነበረው ሁለተኛው የአይ ኤስ የሽብር ቡድን ደግሞ ከቦሳሶ በሶማሌላንድ ሃርጌሳ በኩል ወደ አዲስ አበባ በመግባት የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ሲንቀሳቀስ በብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት በተደረገበት ጥብቅ ክትትል ፋዕድ አብሽር የሱፍ የተባለው የቡድኑ አባል አዲስ አበባ ቦሌ አካባቢ በቁጥጥር ስር እንዲውል የተደረገ ሲሆን ፤ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የዚሁ ቡድን አባላት መካከልም ሙህመድ ጉሀድ ቡዲል የተባለው በሱማሌ ክልል በአፍዴር ዞን ምዕራብ ኢሚ ወረዳ በቁጥጥር ስር ዉሏል።

ሌላ በሀገር ውስጥ የአይ ኤስ የሽብር ቡድን አባል የሆነ ሰይድ ዑመር ሸበሺ የተባለው በፀጥታ አካላት በአዋሽ አካባቢ በቁጥጥር ስር እንዲውል ተደርጓል።

እነዚህ አሸባሪዎች የጥፋት ተለዕኮቸውን ለማስፈፀም የሚጠቀሙባቸው የግንኙነት መሳሪያዎችና ሌሎች ቁሳቁሶች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል።

የሸብር ቡድኖችን በመከታተል በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ለማድረግ በተካሄደው ሰፊ የኦፕሬሽን ስራም የተለያዩ የፌዴራልና የክልል የፀጥታ አካላት እንዲሁም የተለያዩ ሃገራት አጋር የመረጃ ተቋማት ድጋፍ አድርገዋል፡፡ በተለይም ደግሞ የጁቡቲ፣ የሶማሊላንድ፣ የፑንትላንድ የአሜሪካ፤ የጣሊያን፣ የፈረንሳይና የስፔን የመረጃ ተቋማት እገዛ ማድረጋቸውን ብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት በመግለጫው አሳውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አግልግሎት በከፍተኛ ክትትል ያገኛቸውን መረጃዎች ለአሜሪካ፣ ለአውሮፓ፤ ለመካከለኛው ምስራቅ እንዲሁም ለአፍሪካና ለኤዢያ በአጠቃላይ 16 ለሚሆኑ ሀገራት ከተያዙት የሽብር ቡድኖች ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የተደረሰባቸውን የሽብር ቡድኑ ህዋስ አባላት በሀገራቱ እንደሚገኙ የሚያረጋግጥ የመረጃ ልውውጥ በማድረግ የበኩሉን ድርሻ ተወጥቷል።

አሸባሪዎቹ በሀገራችን ህዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች፤ ሆቴሎች፤ በመንግስትና በግል ተቋማት እንዲሁም የሃይማኖት ክብረ ባዓላት በሚከበርባቸው ስፍራዎች በፈንጂ ፍንዳታና በተኩስ የታጀበ የሸብር ጥቃታ በመፈፀም በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመት ለማድረስ ተዘጋጅተውበት የነበረው የሽብር ጥቃትም የከሸፈው በህብረተሰቡ ከፍተኛ ተሳትፎ መሆኑን ብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት አስታውቋል።

በቀጣይም የሽበር ቡድኑ በሀገራችን ጥቃት ለመፈፀም ካለው ዝግጅት አንጻር ህዝባችን ይሄን ተገንዝቦ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደረግና የተለየ ነገር ሲመለከትም በአካባቢው ላለ የፀጥታ አካል መረጃ በመስጠት የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለፅ፤ ብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አግልግሎት በሀገራችንና በህዝባችን ብሄራዊ ጥቅምና ደህንነት ላይ የሚቃጡ ማናቸውንም የሽብር ጥቃቶች አስቀድሞ በማወቅ አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ከምንግዜውም በላይ ዝግጁ መሆኑን ገልፆ፤ የህዝቡ ድጋፍ እንዳይለየው ጥሪ አቅርቧል።