የደቡብ ክልል ምክር ቤት በሁለት አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት በ202ኛ መደበኛ ስብሰባው በሁለት አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ።

ምክር ቤቱ የሲዳማ ዞንን በክልል የመደራጀት ህዝበ ውሳኔ ለማካሄድ የማስፈፀሚያ ፕሮጀክት ማቋቋሚያ ደንብ ላይ ተወያይቷል።

ጥያቄው ለክልሉ ምክር ቤት ቀርቦ ጉዳዩን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መርምሮ ህዝበ ውሳኔ እንዲደራጅ ቀን በቆረጠው መሰረት፥ ውሳኔውን የሚመራ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት የሚቋቋምበት ደንብን በዝርዝር ተመልክቶታል።

በዚህም በቅድመ ህዝበ ውሳኔ፣ በህዝበ ውሳኔና በድህረ ህዝበ ውሳኔ ሊከናወኑ በሚገባቸው ተግባራት ላይ እና በፕሮጀክት ጽህፈት ቤቱ አደረጃጀት ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

የፕሮጀክት ጽህፈት ቤቱ ተጠሪነቱ ለክልሉ ምክር ቤት ሆኖ በእውቀት፣ በክህሎት እና በመልካም ስነ ምግባር የታነፁ አመራሮች እና ባለሙያዎችን በመመደብ ተግባሩን ሀላፊነት በተሞላበት ሁኔታ እንዲመሩትም ውሳኔ አሳልፏል።

ከዚህ ባለፈም ምክር ቤቱ በሁለተኛ አጀንዳው የወላይታ ዞን የወጣቶች መልካም ስብዕና ማዕከልን ለማቋቋም የቀረበውን ፕሮጀክት በዝርዝር ገምግሟል።

ማዕከሉ የወጣቶችን ስነ ምግባር ለመገንባት እና በሀገር የልማት እና የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት ላይ የበኩሉን አስተዋጽኦ የሚያደርግ በመሆኑም የተጠየቀው የግንባታ ቦታ ተግባራዊ እንዲሆንም ወስኗል። መረጃው የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት ነው።