የኢጋድ አባል ሃገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ተወያዩ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በኒውዮርክ እየተካሄደ ከሚገኘው 74ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ጎን ለጎን በኢጋድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊቀመንበርነታቸው የአባል ሃገራት ሚንስትሮች ስብሰባ በመጥራት በጋራ መክረዋል።

በውይይቱ የአባል ሃገራት ሚኒስትሮች የኢጋድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባል ሆነው የተቀላቀሉትን የደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር እንዲሁም የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በተዘጋጀ የእራት ፕሮግራም ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አውት ዴንግ አኩይ በሃገራቸው የሠላም ሂደት የደረሰበትን ዝርዝር ሂደት አስረድተው፥ አባል ሃገራት ድጋፋቸውን እንዲሠጡ ጠይቀዋል።

አዲሱን የሱዳን ካቢኔ የተቀላቀሉት የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስማ አብደላ በበኩላቸው፥ የአካባቢው ሃገራትና ኢጋድ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንዲሠጣቸው ጠይቀዋል።

የአባል ሃገራት ሚኒስትሮች አፍሪካዊ መፍትሄ ለአፍሪካዊ ችግሮች በሚለው መሠረት ሁለንተናዊ ድጋፋቸውን ለመስጠት ቃል ገብተዋል።

በዝግጅቱ የጂቡቲ፣ የሱዳን፣ የደቡብ ሱዳን፣ የሶማሊያና የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እንዲሁም፥ የኬንያና ኡጋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታዎች መገኘታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት አስታውቋል።