ያልተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በተመለከተ ሊደረግ የነበረው ውይይት ተራዘመ

ከውጭ ሀገራት የመጡና ሀገር ውስጥ ያሉ ያልተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በተመለከተ ሊደረግ የነበረው ውይይት ያለስምምነት ተራዘመ፡፡

ቀደም ሲል በፈረሙት የቃል ኪዳን ስምምነት መሠረት ለውይይት የተገናኙት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድና የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይቱ ይካሄድ-አይካሄድ በሚለው ውሳኔ ላይ የተከራከሩ ሲሆን፣ በመጨረሻም ውይይቱ እንዲራዘም ወስነዋል፡፡

ዋልታ ያነጋገራቸው የኦብኮ፣ መኢአድ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ኮንግረስ ፓርቲ አመራሮች በቦርዱ ላይ የነበራቸው እምነት መሸርሸሩን ገልጸው፣ በተለይም በህጉ ላይ ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች 10 ሺህ መስራች አባላት እንዲሁም ለክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች 4 ሺህ መስራች አባላት እንዲኖራቸው ማስገደዱ በፓርቲዎቹ ቅሬታ አስነስቷል፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፀደቀው የምርጫ ህግ 32 አንቀጾች እንዲሰረዙ እና 50 አንቀጾች ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ በውይይቱ ወቅት ተስማምተው እንደነበረ የገለጹት የፓርቲዎቹ አመራሮች፣ ስምምነቱ ሳይፈጸም መጽደቁን አንስተዋል፡፡

የፓርቲዎቹን ቅሬታ በማስመልከት ጥያቄ የቀረበበት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ መሆን አልቻለም፡፡

የህግ አማካሪና ጠበቃ የሆኑት አቶ አምሃ መኮንን ለዋልታ በሰጡት አስተያየት የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ህጉ ላይ መስተካከል አለበት የሚሉት ጉዳይ ካለ እንዲስተካከል በየደረጃው ግፊት ማድረግ እንደአማራጭነት የሚቀርብ ሃሳብ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡