ፌዴራል ፖሊስ በቅርቡ የተከበሩት በዓላት በሰላም እንዲጠናቀቁ ላበረከቱት አስተዋፆ ህዝቡንና የፀጥታ አካላትን አመሰገነ

በ2011 አ/ም መጨረሻ እና በአዲሱ አመት መጀመሪያ ላይ የተከበሩ በአላት በሰላም ለመጠናቀቃቸው መላው የፀጥታ ሀይልና ህብረተሰቡ ላደረጉት አሰተዋፅኦ ፌዴራል ፖሊስ አመሰገነ፡፡

ፌዴራል ፖሊስ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ለእሬቻ በአል ስኬትም የአዲስ አበባ ህዝብና የበአሉ ተሳታፊዎች ላደረጉት አሰተዋፅኦ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

መግለጫዉን የሰጡት በፌዴራልፖሊስ የወንጀል ዘርፍ ሃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ ህዝቡ እንደሃገር የሚከበሩ በአላትና አህጉራዊና አለምአቀፋዊ ስብሰባዎች በሚኖሩበት ጊዜ ለዝግጅቶቹ ስኬቶችና በሰላም መጠናቀቅ የሚያደርገዉን አስተዋፅኦ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አሳሳቢ እየሆነ የመጣዉ ህገ-ወጥ የጦር መሳርያ ዝዉዉር ችግርን ለመፍታት የሚከናወነዉ ስራ ዉጤታማ ቢሆንም የችግሩን አሳሳቢነት የሚረዳዉ ፖሊስ ህብረተሰቡ አሁንም ከጎኑ እንዲቆም ጥሪ አቅረቧል፡፡

በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች እየተነሱ ባሉ ግጭቶች ሰላማዊ ሰዎችና ህግ አስከባሪዎች በስፋት ለጉዳት እየተዳረጉ መሆናቸዉንም ፖሊስ ገልጿል፡፡

ህዝብና ህዝብ መቼም ቢሆን ተጋጭቶ አያዉቅም ያለዉ ፖሊስ ለራሳቸዉ ሲሉ ችግሮችን የሚፈጥሩ አካላት ከድርጊታቸዉ እንዲታቀቡ ፖሊስ ጠይቋል፡፡

በያዝነዉ አመት ከሚከናወኑ ስራዎች የፌዴራል ፖሊስን ማዘመን እንደሚገኝበት የተናገሩት ሃላፊዉ በምድርና በአየር ጭምር ደረጃዉን በጠበቀ መልኩ ሰራዉን ማከናወን የሚያስችል አደረጃጀት ዕዉን ይደረጋል ብለዋል፡፡