ምክር ቤቱ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አስተላለፈ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አስተላልፏል፡፡

ምክር ቤቱ በ5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ስብሰባው የምክር ቤቱን 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 3ኛ አስቸኳይ ስብሰባ ቃለ ጉባኤ መርምሮ አፅድቋል፡፡

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ መስከረም 26፣2012 ዓ.ም ለህዝብ ተወካዮችና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ መክፈቻ መደበኛ ስብሰባ ላይ ያቀረቡትን እቅድ አስመልክቶ የቀረበውን የድጋፍ ሞሽን በማድመጥ አፅድቋል፡፡

የመድን ስራ ዐዋጅን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ ዐዋጅን መርምሮ ያፀደቀ ሲሆን ፤ በሰው መነገድና ሰዎችን በህገ ወጥ መልኩ ድንበር ማሻገር ወንጀል ለመከላከልና ለመቆጣጠር የቀረበውን ረቂቅ ዐዋጅን ጨምሮ 10 ረቂቅ አዋጆችን ለዝርዝር እይታ እና ምርመራ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል።

 ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ረቂቅ ዐዋጅ ጋር ተያይዞ ከዚህ በፊት በማረሚያቤቶች የሚፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዳይደገሙ ትኩረት መሰጠት እንዳለበት በምክር ቤቱ አባላት ተነስቷል፡፡

በተጨማሪም ከፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ ጋር ለልማት ፖሊሲ ፕሮግራም ማስፈፀሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነት እና ከአረብ ባንክ ለአፍሪካ ኢኮኖሚ ልማት ጋር  የተደረገውን የብድር ስምምነት ለማጽደቅ የቀረቡ ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል።

ከብድር ጋር ተያይዞ ሀገሪቱ የመክፈል አቅሟ በተዳከመበት ወቅት የብድር ስምምነት መፈፀሙ እንዴት ይታያል የሚሉና ብድሮች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ባለጋገጠ መልኩ ስራ ላይ እንዲውሉ ጥንቃቄ እንዲደረግ ሃሳብ ቀርቧል፡፡

ከዚህ በፊት በተፈቀዱ ብድሮች ዙሪያም በቀጣይ በቂ ማብራሪያ እንደሚሰጥና የምክርቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡

ምክርቤቱ በተጨማሪ የአነስተኛ ፋይናንስ ሥራ አዋጅን ለማሻሻል፣ የፌዴራል ድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ስርዓትና ተቋማዊ አደረጃጀትን ለመወሰን ፣የመድን ሥራ አዋጅን ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል፡፡