ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሊቢያ ከፍተኛ ምክር ቤት ልዑካንን በፅህፈት ቤታቸው አነጋገሩ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በሊቢያ ከፍተኛ ምክር ቤት ሊቀ-መንበር ካሊድ አል-ሚሽሪ የተመራውን ልዑካን ቡድን በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

የሊቢያ ከፍተኛ ምክር ቤት ሊቀ-መንበር ካሊድ አል-ሚሽሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኖቤል ሰላም ሽልማትን በማግኘታቸው ደስታቸውን ከመግለጻቸውም ባሻገር በአመራራቸው ያስገኟቸውን ለውጦች አስመልክቶ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

አክለውም በሊቢያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ለሚደረገው ቀጣይ ጥረት እገዛ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም ሊቢያ ያለችበትን አሳሳቢ ሁኔታ አስመልክቶ ሀሳባቸውን ገልጸው ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ እንዲሁም ክልላዊ ተቋማት አማካኝነት ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን አስታውቀዋል።

ሊቢያውያን በሀገራቸው ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ እንዲበረቱና በአንድነት ጥረት እንዲያደርጉም ማሳሰባቸውን ከጠቅላ ሚኒስትር ፅ/ቤት ያገኘነው ዘገባ ያመለክታል፡፡