አገራት ለካንሰር ህክምና መስጫ ማዕከላት መስፋፋት ትኩረት እንዲሰጡ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 18/2008(ዋኢማ)-አገራት ካንሰርን ከመከላከል ባለፈ ለመስኩ ህክምና መስጫ ማዕከላት መስፋፋት ትኩረት እንዲሰጡ ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ ጠየቁ።

የማህፀን በር ጫፍ፣ የጡትና የፕሮስቴት ካንሰር 10ኛ ጉባዔ ትናንት በአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን መካሄድ ጀምሯል።

ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ይህን ያሉት የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) አባል አገራት ቀዳማዊት እመቤቶች መድረክ በካንሰር ላይ ሲመክር ነው።

ምክክሩ "ሴቶችን በኢኮኖሚ በማጎልበት ካንሰርን በአፍሪካ መግታት" በሚል መሪ ሃሳብ ነው የተካሄደው።

የጡትና የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ሴቶችን ከሚያጠቁ የካንሰር ዓይነቶች በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።

በማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ምክንያት በየሁለት ደቂቃው አንዲት ሴት ለህልፈት እንደምትዳረግ የመስኩ ጥናቶች ያሳያሉ።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ሳቢያ በየዓመቱ ከ250 ሺህ በላይ ሴቶች ለህልፈት እንደሚዳረጉም ተጠቁሟል።

እንደ ጎርጎሮሳውያን የጊዜ ቀመር በ2011 በዓለም አቀፍ ደረጃ 508 ሺህ ሴቶች በጡት ካንሰር ሳቢያ ህይወታቸውን ተነጥቀዋል።

የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ቀዳማዊ እመቤቶች መድረክም ካንሰር እያደረሰ ያለው ጉዳት አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ነው ያነሳው። 

የወቅቱ የኮሜሳ ቀዳማዊ እመቤቶች መድረክ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሮማን በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ካንሰር የሚያደርሰውን ጉዳት ለመግታት ከመከላከል ጎን ለጎን የህክምና መስጫ ተቋማት ማስፋፋት ይጠበቅባቸዋል። 

ይህን ለማሳካት ደግሞ አገራት ከዓመታዊ በጀታቸው ለካንሰር ህክምና መስጫ ማዕከላት የሚውል በጀት ሊመድቡ ይገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ የካንሰር ህክምና በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል የተወሰነ ሲሆን በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ ይህን አኃዝ ወደ አምስት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተናግረዋል።

በዚህም ህክምናው ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በጎንደር፣ በመቐለ፣ በጅማ፣ በሀዋሳና በሀረር ከተሞች የሚሰጥ ይሆናል ነው ያሉት።

የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል ከ1996 እስከ 2008 ዓ.ም ከሰጣቸው የካንሰር ህክምናዎች 30 ነጥብ 3 በመቶ ያህሉ የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ታማሚዎች ናቸው።

በሽታው በመላ አገሪቱ ከ100 በሚበለጡ የህክምና መስጫ ማዕከላት እየሰተጠ መሆኑን ገልጸው በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን በሁሉም የአገሪቱ ወረዳዎች እንዲሰጥ ይደረጋል ብለዋል።

ሴቶች ስለ ካንሰር ያላቸውን ግንዛቤ ማሳደግ በሽታውን ለመከላከል ዓይነተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው የገለጹት ደግሞ በኢትዮጵያና በአፍሪካ ኅብረት የመንግሥታቱ ድርጅት የሴቶች ተወካይ የሆኑት ሌቲ ቺዋራ ናቸው።

ካንሰርን ከመከላከል በተጨማሪ ህሙማን ህክምናውን የሚያገኙበት ማዕከላት መገንባት የመንግሥታት ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባልም ብለዋል።

በመድረኩ የሴቶች ኢኮኖሚያዊ አቅም በማጎልበት ካንሰርን መግታት እንደሚገባ የጋራ አቋም ተይዟል።

በዚህ ረገድ የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) የሴቶችን አቅም ለማጎልበት እያደረገ ያለውን ጥረት የሚዳስስ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል።

ጽሁፉን ያቀረቡት የኮሜሳ የሥርዓተ-ፆታና የማህበራዊ ጉዳዮች ክፍል ዳይሬክተር ፒተርስ ሃሞሶንዴ እንዳሉት አባል አገራት የሴቶችን አቅም ለማጎልበት የገቡትን ቃል ሊያረጋግጡ ይገባል።

በኮሜሳ የማቋቋሚያ አዋጅ አንቀጽ 154 እና 155 የሴቶችን ሚና በግልጽ የሚደነግግ ሲሆን አገራትም ለሴቶች እኩል እድሎች በመፍጠር ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን እንዲያሳድጉ የሚል ሀሳብ አካቷል።

አብዛኞቹ ሴቶች ኢኮኖሚያዊ አቅማቸው ጠንካራ ባለመሆኑ የካንሰር ህክምናን ለማግኘት እንደሚቸገሩ ነው የተናገሩት።

የመስኩን ህክምና አቅርቦት ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ የሴቶች ኢኮኖሚያዊ አቅም ማጎልበት ሊተኮርበት ይገባል ብለዋል።

የማህፀን በር ጫፍ፣ የጡትና የፕሮስቴት ካንሰር 10ኛ ጉባዔ ከትናንት ጀምሮ ለአራት ቀናት በአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የመሰብሰቢያ አዳራሽ መካሄዱን ይቀጥላል።( ኢዜአ)