የኢትዮጵያ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም በ33 የአፍሪካ ሀገራት በተሞክሮነት ተወስዷል

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20/2008(ዋኢማ)-የዓለም ጤና ድርጅት ኢትዮጵያ የዘረጋችው የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ለአፍሪካውያን በምርጥ ተሞክሮነት የሚወሰድ ነው ብሏል።

በደርጅቱ የአፍሪካ የድንገተኛ በሽታዎች ዳይሬክተር ዶክተር ኢብራሂም ሶሲፋል እንዳሉት፥ ሃገሪቱ የጤና አገልግሎትን ለሁሉም ህብረተሰብ ለማዳረስ የጀመረችው እንቅስቃሴ ውጤታማ አድርጓታል።

አፍሪካውያን በጤናው ዘርፍ ከኢትዮጵያ የወሰዱትን ምርጥ ተሞክሮ ለመተግበር እንዲንቀሳቀሱም ዶክተር ኢብራሂም አሳስበዋል።

በዓለም የጤና ድርጅት የአፍሪካ ተወካይ ዶክተር ማቲሺዲሶ ሞኢቲ በበኩላቸው ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችው የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም መንግስት ለጤናው ዘርፍ የሰጠውን ትኩረት ማሳያ ነው ብለዋል።

የአፍሪካ አገራትም በጤናው ዘርፍ የኢትዮጵያን ልምድ በመውሰድ የዕቅዳቸው አካል አድርገው ሊተገብሩት ይገባል ነው ያሉት።

በአገሪቱ የጤና ሽፋን ለማዳረስ በገጠርና በከተማ ከ39 ሺህ በላይ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች መሠማራታቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ከ25 ዓመታት በፊት የነበረው ከ17 ሺህ ያልበለጠ የጤና ባለሙያዎች ቁጥርም በአሁኑ ወቅት ከ180 ሺህ በላይ ደርሷል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶክተር ከሰተብርሃን አድማሱ እንዳሉት የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ቤት ለቤት በሚሰጡት ትምህርት የቤትና የአካባቢ ጤናን በመጠበቅ የተሻለ ለውጥ ተመዝግቧል።

የኢትዮጵያን የጤና ኤክስቴንሽን የተለያዩ የአፍሪካ አገራት እስከ ስድስት ወራት በመቆየት ልምዷን መጋራታቸውን ገልጸዋል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው የኢትዮጵያ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም እስካሁን በ33 የአፍሪካ አገራት በተሞክሮነት ተወስዷል።

ደቡብ ሱዳን፣ ሌሴቶ፣ ስዋዚላንድና ዛምቢያ ፕሮግራሙን ተግባራዊ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ሲሆኑ ናሚቢያ የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞችን በመመልመል ወደ ሥራ ገብታለች።

ሌሎች የአፍሪካ አገራትም የኢትዮጵያን ልምድ ለመቅሰም ጥያቄ ማቅረባቸው ተመልክቷል ።(ኢዜአ)