የጤና ተደራሽነትን በማረጋገጥ አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል

የጤና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የተሰሩት ሥራዎች አመርቂ ውጤት ማስመዝገባቸውን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

መንግስት ባከናወናቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት ህዝቡ በቅርበት የጤና አገልግሎቶችን እንዲያገኝ ማስቻሉን በሚኒስቴሩ የአጠቃላይ ጤና ዘርፍ ዳይሬክተር ተወካይ  ዶክተር ይበልጣል መኮንን ለዋልታ ገልጸዋል፡፡

ከ25 ዓመት በፊት ዜጎች ህክምና ለማግኘት በጣም ይቸገሩና ይሰቃዩ እንደነበር ዶክተር ይበልጣል ያስታውሳሉ፡፡

በተለይም የወሊድ፤ የህፃናትና የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት በቅርበት ለማግኘት በጣም ይቸገሩ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡

አሁን ላይ በጤናው ዘርፍ በተሰሩት ሥራዎች ህብረተሰቡ የመጀመሪያ ደረጃ ህክምናን በየአምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚያገኝበት ዕድል መመቻቸቱን ነው ዶክተር ይበልጣል ያስረዱት፡፡ 

በቀጣይ በማደግ ላሉ ክልሎች የተለየ የጤና አገልግሎት ድጋፍ ሥርዓት መዘርጋቱን አስታውቀዋል ፡፡

ጤና ኬላዎች ፤ከጤና ጣቢያዎችና ከመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ጋር እንዲተሳሰሩ በማድረግ ዜጎች የቀዶ ህክምና አገልግሎት የሚያገኙበት ሁኔታም መመቻቸቱን አብራርተዋል ፡፡

ለዚህም በየክልሎቹ የጤና ቢሮዎችን በማቋቋም፤ የህክምና መስጫ ማዕከላትን በመገንባት፣አስፈላጊ ቁሳቁሶችን በማሟላትና የሰው ኃይል በመመደብ እየተሰራ ነው- ብለዋል ፡፡

ማህበረሰቡን ባሳተፈ መልኩ በተለይም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በመከላከል ረገድ በስፋት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል ፡፡

የጤና አገልግሎት ሽፋንን ከማረጋገጥ በተጓዳኝ ጥራቱን የጠበቀ ህክምና እንዲሰጥም ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡

ታካሚ ተኮርና ወጭ ቆጣቢ ህክምና እንዲያገኙም እየተሰራ ነው ብለዋል፤ ዶክተር ይበልጣል፡፡

የማህበረሰብ ጤና አገልግሎት በመዘርጋትም ዜጎች በየጊዜው የተወሰነ ገንዘብ በመቆጠብ የጤና አገልግሎት የሚያገኙበት ሥርዓትም መዘርጋቱን አስታውቀዋል፡፡

በጤና ኬላ፣ በጤና ጣቢያና በአጠቃላይ ሆስፒታል የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና ሽፋን 100 በመቶ መድረሱን አስታውቀዋል ፡፡

የስነ አዕምሮ፣ የእናቶችና የህፃናት ህክምና፣የካንሰር፣የልብና ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የድንገተኛ ህክምና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውም ነው ያመለከቱት ፡፡

መንግስት የግሉን ዘርፍ በማሳተፍና በመደገፍ እንደሚሰራም ነው የተጠቆመው፡፡

የውዳሴ ዲያግኖስቲክ ላቦራቶሪ ማዕከል ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳዊት ሀይሉ የጤና አገልግሎትን ለማሳደግ የበኩላቸውን ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ማዕከሉ በየዓመቱ ‹‹ጳጉሜን ለጤና›› በሚል መርሀ ግብር ለዜጎች ነፃ የህክምና አገልግሎት እንደሚሰጡ አስታውቀዋል፡፡

ዘንድሮ ለሰባተኛ ጊዜ የነፃ አገልግሎቱን እንደሚሰጥ ጠቁመው እስከ አሁንም ለ15 ሺ ያህል ዜጎች አገልግሎቱን ሰጥቷል ብለዋል፡፡

ማዕከሉ ከመንግስት የህክምና ተቋማት የህክምና ማዘዣ ለተሰጣቸው ታማሚዎች በየዓመቱ ነፃ የኤም አር አይና የሲቲ ስካን ህክምና እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡