በዓላትን በሰላም ለማሳለፍ ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ተገለጸ

እሁድና ሰኞ ለሚከበሩት የዘመን መለወጫና የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓላት ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከያና መቆጣጠር ባለስልጣንና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከያና መቆጣጠር ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ደጋፊ የሥራ ሂደት አቶ ሰለሞን መኮንን ለዋልታ እደገለጹት በዓሉን በሰላምና ከአደጋ ነፃ በሆነ መልኩ ለማክበር እንዲቻል ሕብረተሰቡ ኤሌክትሪክ፣የከሰል ምድጃ ሲጠቀም እና  ጧፍና ሻማ በሚያበራበት ጊዜ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ መኪናዎችን ደርቦ በማቆም መንገድ ከመዝጋት፣ የኤሌክትሪክ ሶኬቶችን ደራርቦ ከመጠቀም መቆጠብ እንደሚገባ አቶ ሰለሞን ተናግረዋል፡፡ በደመራ ወቅት ችቦ ሲለኮስ ተገቢውን ጥንቃቄ በመቀድረግ አደጋን ለመመቀነስና ለመከላከል መትጋት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

አደጋዎች ቢከሰቱ ለባለስልጣኑ በፍጥነት መረጃዎችን በማድረስ የ24 ሰዓት አገልግሎት ለመስጠት ኤጄንሲው በተጠንቀቅ መቆሙን አቶ ሰለሞን አክለው ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኑነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ በበኩላቸው በዓላቱን በሰላም አክብሮ ለማለፍ እንዲቻል ሕብረተሰቡን ያካተተ የውይይት ዝግጅት መደረጉን ገልፀዋል፡፡

ሕብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ወንጀልን ለመከላከልና ሰላምን ለማስፈን በተከናወኑት ተጨባጭ ተግባራት በ2008 ዓ.ም. ብቻ ወንጀልን በ26 በመቶ ለመቀነስ መቻሉን በግምገማ ማረጋገጣቸውን ኮማንደር ፋሲካ ተናግረዋል፡፡

ሕብረተሰቡ ከፖሊስ ጋር በመሆን በሚያደርገው ንቁ ወንጀልን የመከላከል ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከያና መቆጣጠር ባለስልጣንና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለመላው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በዓሉ የሰላም፣ የደስታና የብልጽግና እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡

የእሳትና ድንገተኛ አደጋ ቢያጋጥም በስልክ ቁጥር 011 155 53 00 እና 011 156 86 01 እንዲሁም በነፃ የስልክ ጥሪ 939 መጠቀም ይችላሉ፡፡ ለፖሊስ ኮሚሽን ደግሞ 011 111 01 11 ወይም ነፃ የስልክ ጥሪ 991ን መጠቀም ይቻላል፡፡