ሙስሊሙ ማህበረሰብ በዓሉን ሲያከብር በመተሳሰብና በመደጋገፍ መሆን አለበት- ሀጂ መሀመድ አሚን

 

መላው የእስልምና እምነት ተከታይ የኢድ አል አደሀ አረፋ በዓልን ሲያከብር የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና እርስ በእርስ በመተጋገዝ መሆን እንዳተለበት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ገለፀ።

1 ሺህ 437ኛው የኢድ አል አደሀ አረፋ በዓል በመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ይከበራል።

በዓሉን አስመልክተው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሀጂ መሀመድ አሚን ጀማል በሰጡት መግለጫ፥ መላው የእስልምና እምነት ተከታይ በዓሉን ሲያከብር የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና እርስ በእርስ በመተጋገዝ መሆን ይኖርበታል ብለዋል።

በተጨማሪም ምእመኑ መልካም ህዝብ በመሆን ራሱንና ሀገሩን ለማሳደግና የህዝቡን ሰላም ለመጠበቅ ከመቼውን ጊዜ በለላይ እንዲንቀሳቀስም ጥሪ አቅርበዋል።

ፕሬዘዳንቱ ሀጂ መሀመድ አሚን ጀማል በዓሉን አስመልክተው ባስተላለፉት መልእክት፥ በአሉ የደስታ በዓል በመሆኑ ያለው ከሌለው ጋር በመካፈል ማሳለፍ ይኖርበታል ብለዋል።

ነብዩ ኢብራሂም ልጃቸው እስማኤልን በአላህ ትእዛዝ ለመስዕዋት ሲያዘጋጁ በምትኩ ሙክት በግ መቅረቡን የሚያስታውስ በመሆኑ የመስዋዕት በዓል ተብሎም ይከበራል ኢድ አል አድሃ ወይንም አረፋ በዓል።

በአሉ በመላው ዓለም የእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ከሚከበሩ አበይት በዓላት መካከል አንዱ ነው።

በዓሉ ሌላም ሃይማኖታዊ መልእክት አለው የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፥ አዳምና ሄዋን ከገነት ወጥተው ለረጅም ዘመናት ተለያይተው ከቆዩ በኋላም በአራራት ተራራ ላይ መገናኘታቸው የሚዘከርበት በዓል ነው ብለዋል።

ዘንድሮም 1 ሺህ 437ኛው የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል በመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በደማቅ ስነ ሰርአት ነው የሚከበረው።

ከፍተኛ ቁጥር ያለው ምእመንም ወደ አራፋት ተራራ በመውጣት ይመለሳሉም።

በመንገዳቸው ላይም የተለያዩ እርዶችን እየፈጸሙ የሚያከብሩበት ደማቅ በአል መሆኑን ነው ፕሬዘዳንቱ ሀጂ መሀመድ አሚን ጀማል የገለጹት።

የእምነቱ ተከታዮችም በዓሉን በሚያከብሩበት ጊዜ የተቸገሩ ወገኖችን በርዳትና በመንከባከብ፤ በህመም ላይ የሚገኙ ወገኖችን በመጠየቅ የእርስ በእርስ ባህላቸውን በማጠናከር መሆን ይኖርባቸዋል ሲሉ አስታውቀዋል።

በዘንድሮ የአረፋ በዓል 8 ሺህ ኢትዮጵያውያን ሃጃጆች ወደ ተቀደሰውና ወደ ተከበረው ምድር የተጓዙ መሆናቸውን የገለጹት ፕሬዘዳንቱ፥ ምንም አይነት እንግልት ሳይደርስባቸው እንዲመለሱ ምክር ቤቱ ሃይማኖታዊ ግዴታውን በብቃት እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ኤፍቢሲ ዘገባ በሀገር ውስጥ ያለው ሙስሊሙ ህብረተሰብም ወንድማማችነቱን ጠብቆ ሀገሪቷ ለጀመረችው የእድገትና የልማት ጉዞ የበኩሉን እንዲወጣ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።