ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ 11 አዳዲስ የትምህርት ፕሮግራሞች ሊከፍት ነው

ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ በ2009 ዓመተ ምህረት 11 አዳዲስ ፕሮግራሞች ለመክፈት በዕቅድ መያዙን አስታወቀ ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕረዚዳንት ዶክተር ዛይድ ነጋሽ ከዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳስታወቁት ፤ዩኒቨርሲቲው ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት ወሳኝ ሚና ያለው የተማረ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ የሚያደርገውን ጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መጥቷል ፡፡

በዚሁም መሰረት በአዲሱ የትምህርት ዘመን 11 በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር መዘጋጀቱን አስታውቋል ፡፡

ከነዚሁም ውስጥ ጋዜጠኝነትና ማስ ኮሙኒኬሽን፣ ሎጂስቲክስ እና ሳፕላይ ማኔጅመንት፣ላባላቶሪ ቴክኒሺያንነት፣ሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ፣አርባን ኢንጂነሪንግ ፣ግሪካልቸራል ኢኮኖሚክስ ፣ ፉድ ሳይንስና ፖስት ሃርቨስቲንግ ቴክኖሎጂ በመጀመሪያ ዲግሪ የሚከፈቱ ናቸው ብለዋል፡፡

እንደዚሁም በሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር የሚከፈቱት ደግሞ ሳይንስና ፐብሊክ ሄልዝ ፣ኢኮኖሚክስ፣ፊዚክስ እና ጂኦግራፊ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

ለነዚህ አዳዲስ ፕሮግራሞች በመምህራን በኩል የተሟላ ቢሆንም በተማሪዎች በኩል ካልተሟላ ሁሉም ፕሮግራሞች ላይከፈቱ ይችላሉ ብለዋል፡፡

ዘንድሮ የተመደቡላቸው 5 ሺ 600 ተማሪዎች በጥቅምት ወር የሚቀበሏቸውን ጨምሮ ከ16ሺ በላይ ተማሪዎች የሚያስተናግዱ መሆናቸውን ዶክተር ዛይድ አስታውቀዋል፡፡

በ2004 ዓመተ ምህረት በ13 የትምህርት ፕሮግራሞች በ960 ተማሪዎች ብቻ የጀመረው ዩኒቨርሲቲው ከአራት ዓመት በኋላ የመደበኛ ተማሪዎች ቁጥር ወደ 20ሺ ከፍ ለማድረግ መታቀዱን አመልክተዋል፡፡

በአዲሱ የትምህርት ዘመን የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ በሰው ኃይልና በቁሳቁስ የሟሟላት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ሰባት የላባላቶሪ ብሎኮችን በመገንባት በዘመናዊ መሳሪያዎች ከሟሟላታቸውም በተጨማሪ በርካታ ወርክሾፖች ያሏቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በ2009 ዓመተ ምህረትም የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማጠናከር በተመደበላቸው ግማሽ ቢሊየን ብር ተጨማሪ የማስፋፊያ ስራዎችን እንደሚካሄድም ገልጸዋል ፡፡

ከዚህ በፊት የትምህርት አሰጣጥ ዘዴ ከአስተማሪ ወደ ተማሪ መስጠት ነበር ያሉት ዶክተር ዛይድ ፤አሁን ግን ተማሪ ተኮር ሆኖ አሳታፊ ስራ እየተካሄደ መሆኑን አስረድተዋል ፡፡

ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በቡድን ተደራጅተው እርስ በርስ የሚሟሟሩበት አካሄዳቸው በሀገር ደረጃ በሞዴልነት የመጠቀስ መሆኑን ዶክተር ዛይድ አስታውቀዋል፡፡

ይህም ባለፈው ዓመት ብቻ ከ17 የአገራችን ዩኒቨርሲቲዎች ተሞክሮ ለመቅሰም ዩኒቨርሲቲውን መጎብኘታቸውን አስረድተዋል፡፡

የትምህርት ጥራት በቀጣይነት ለማረጋገጥና ብቁ ተማሪዎችን ለማፍራት ጥረቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ፕረዚዳንቱ አረጋግጠዋል፡፡