ድርጅቱ ከ5 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ህፃናትን የተመጣጠነ ምግብ ተጠቃሚ አደረገ

የአሜሪካ ዓለም ዓቀፍ የልማት ተራድዖ ድርጅት የእናቶችና ህፃናትን ጤና ለመጠበቅ ባደረገው ድጋፍ ከአምስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን በላይ ህፃናት የተመጣጠነ ምግብ ማግኘታቸው ተመለከተ፡፡

ዛሬ በሂልተን ሆቴል በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ እንደተገለፀው የተራድዖ ድርጅቱ በህፃናት አድን ድርጅት (ሴቭ ዘ ችልድረን) አማካኝነት ህፃናትና እናቶች በቅድመና ድህረ ወሊድ ወቅት የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ ለአምስት ዓመት በተተገበረው ፕሮጀክት አምስት ሚሊዮን 672ሺ ህፃናት የተመጣጠነ ምግብ አግኝተዋል፡፡

ለፕሮጀክቱም የአሜሪካ ዓለም ዓቀፍ የልማት ተራድዖ ድርጅት 50 ሚሊዮን ዶላር ወጭ ማድረጉ በመድረኩ ተገልፃል፡፡ በውጤቱም በአራት ክልሎች በተመጣጠነ ምግብ እጥረት የሚሰቃዩ ህፃናትን በ16 በመቶ ለመቀነስ ተችሏል ተብሏል፡፡ የተመጣጠነ ምግቡ ከፅንስ እስከ ሁለት ዓመት ዕድሜ ድረስ መሰጠቱም ነው የተመለከተው፡፡

ፕሮጀክቱ በአማራ፣ኦሮሚያ፣ትግራይና የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል መተግበሩን በኢትዮጵያ የህፃናት አድን ድርጅት ዳይሬክተር ሚስተር ጆን ግራም ገልፀዋል፡፡ በዚህም በ116 ወረዳዎች ላይ ህፃናትና እናቶች የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡

እአአ ከ2011 እስከ 2016 የተተገበረው ፕሮጀክት የኢትዮጵያ መንግስት የነደፈውን ብሔራዊ የተመጣጠነ ምግብ መርሀ ግብር ማገዙን ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል፡፡ ይህም በአስተማማኝ፣በተቀናጀና በትክክለኛ መረጃ ላይ መሰረት አድርጎ መተግበሩን ተናግረዋል፡፡

ህፃናት የተመጣጠነ ምግብ አግኝተው እንዲያድጉ የአሜሪካ ዓለም ዓቀፍ የልማት ተራድዖ ድርጅት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ በኢትዮጵያ የልማት ተራድዖ ድርጅቱ የተልዕኮ ዳይሬክተር ሚስ ሌስሊ ሪድ ተናግረዋል፡፡

ተራድዖ ድርጅቱ በህፃናት አድን ድርጅት በኩል ባደረገው ድጋፍ የተመዘገበው ውጤትም የሚበረታታና የሚደነቅ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ድርጅቱ በቀጣይም አስፈላጊውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የእናቶችና ህፃናት ጤና ዳይሬክተር ዶክተር ኤፍሬም ተክሌ በበኩላቸው የተመጣጠነ ምግብ በቤተሰብ ደረጃ እንዲኖር መንግስት ራሱን የቻለ መርህ ግብር ቀርፆ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የህፃናት አድን ድርጅት ተግባርም መንግስት ለነደፈው ፕሮግራም ትልቅ መሳሪያ ሆኖ ማገዙን ነው ዶክተር ኤፍሬም ያስረዱት፡፡ በተለይም ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ለስቃይና ለህልፈተ ህይወት እንዳይዳረጉ መንግስት የጀመረውን ጥረት በማገዝ በኩል ሚናው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

በመድረኩ እንደተገለፀው በፕሮጀክቱ የአምስት ዓመት ቆይታ የተመጣጠነ ምግብ የሚያገኙ ህፃናት፣ ተገቢውን የህክምና ክትትል የሚያደርጉ ወላድ እናቶች ቁጥር ጨምሯል፡፡ የተለያዩ የጤና ክብካቤና የገቢ ማሳደጊያ ስልጠናዎችም ተሰጥተዋል፡፡