በጋምቤላ ክልል ለትምህርት ፍትሃዊ ተደራሽነት ሁሉንም ያሳተፈ ስራ እየተከናወነ ነው—ርዕሰ መስተዳደር ጋትሉ ዋክ ቱት

በጋምቤላ ለትምህርት ጥራትና ፍትዊነት በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላትንና የህዝቡን ተሳትፎ በማጠናከር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ጋትሉዋክ ቱት ገለጹ።

በስነ-ምግባርና በእውቀት የታነጸ ዜጋ ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ከመምህራንና የትምህርት ባለሙያዎች በተጨማሪ የወላጆችና በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላት ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ የክልሉ መምህራን ገልጸዋል።

በጋምቤላ ከተማ እየተካሔደ ባለው የመምህራንና የትምህርት ባለሙያዎች ውይይት ላይ ርዕሰ መስተዳደሩ እንዳመለከቱት በክልሉ የትምህርትን ፍትሀዊ ተደራሽነትና ጥራት በማጎልበት የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ የመገንባቱ ሂደት ተጠናክሮ ይቀጥላል።

ርዕሰ መስተዳደሩ"ከክልል እስከ ገጠር ቀበሌዎች ያለው የትምህርት ሽፋን የተሻለ ቢሆንም  ከባድ ፈተና የሆነው ግን የጥራት ጉዳይ ነው" ብለዋል።

ከአዲሱ የትምህርት ዘመን ጀምሮ በትምህርት ጥራትና ልማት እምርታዊ ለውጥ ለማምጣት የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

“ ማህበረሰቡም ልጆቹን በመከታተል በመልካም ስነ-ምግባርና እውቅት እንዲታነጹ መስራት አለባቸው"ብለዋል ።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል መምህር ቴር ዮንግ በሰጡት አስተያየት "የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ብቃት ያለውና መልካም ስነ-ምግባር የተላበሰ ዜጋ የማፍራቱ ስራ በመምህራን ብቻ ውጤታማ ሊሆን አይችልም " ብለዋል።

ተማሪዎችን ማብቃት የሚቻለው  መምህራን ፣ ወላጆችና የአመራር አካላት ተባብረውና ተቀራርበው መስራት ሲችሉ መሆኑንም መምህሩ ተናግረዋል።

ሌላዋ የውይይቱ ተሳታፊ መምህርት ኑሪያ ያሲን እንደገለጹት በእውቀትና በስነ ምግባር የተገነባ ዜጋ ለመፍጠር የሚቻለው የሁሉም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረት ሲታከልበት ነው።

የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ብቁ ሀገር ተረካቢ ዜጋ መቅርጽ የሚቻለው መምህራን፣ ወላጆችና በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላት በጋራ ተቀናጅተው መስራት ሲችሉ መሆኑንም መምህርቷ ተናግረዋል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ቱት ጆክም የህዝብ፣ የመንግስትና የድርጅት ክንፎችን በትምህርት ስራው በማሳተፍ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና የመጠነ ማቋረጥና መድገም ችግሮችን ለመቀነስ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በ2009 የትምህርት ዘመን የተማሪ ወላጆች በትምህርት ሥራው ላይ በባለቤትነት እንዲሳተፉ የተጠናከረ የንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ ነው ብለዋል ።

የጋምቤላ ከተማ መስተዳድርን ጨምሮ በ14 ወረዳዎች ከ4 ሺህ 500 መቶ በላይ የአንደኛ፣የሁለተኛ ደረጃና የመሰናዶ ትምህርት ቤቶች መምህራንና ሱፐርቫይዘሮች በ2009 የትምህርት እቅድና በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ እየተወያዩ ይገኛሉ /ኢዜአ/ ።