አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ የህግ የክብር ዶክትሬት ተቀበሉ

 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ ከደቡብ ኮሪያው የሐንዶንግ ግሎባል ዩኒቨርሲቲ የሕግ የክብር ዶክትሬት መቀበላቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

አፈ ጉባዔ አባዱላ የክብር ዶክትሬቱ የተሰጣቸው ወታደራዊውን የደርግ ሰራዊት ለመደምሰስ በተደረገው የትጥቅ ትግል ከመሳተፍ ጀምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች በተለይም በመከላከያ ሚኒስትርነት፣ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንትነትና በአሁኑ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔነት ላበረከቱት አስተዋጽኦ መሆኑ ተገልጿል።

የሐንዶንግ ግሎባል ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሱን ሂዩንግ ቻንግ፥ አባዱላ ለረጅም ጊዜያት ለአገራቸው ሠላም፣ ዴሞክራሲና ልማት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያበረከቱ በመሆናቸው የክብር ዶከትሬቱ ተሰጥቷቸዋል ብለዋል።

አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ በስነ-ስርዓቱ ላይ ዩኒቨርሲቲው ለሰጣቸው እውቅና አመስግነው፤ እውቅናው የእርሳቸው ብቻ ሳይሆን በረዥሙ የትጥቅ ትግልና ባለፉት 25 ዓመታት በኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ለውጥ ለማምጣት ለታገሉ፣ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት የተሰጠ እንደሆነ ተናግረዋል።

ዩኒቨርስቲው ከአገሪቱ ዜጋ ውጪ ሕዝባዊ አገልግሎት ለሰጠ ግለሰብ የክብር ዶክትሬት ሲሰጥ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ምንጭ፦ ኢዜአ