የኢሬቻ በዓልን ለማክበር ዝግጅቶች ተጠናቀዋል

የኢሬቻ በዓልን ነገ በቢሾፍቱ ከተማ በሆራ አርሰዲ ሐይቅ ለማክበር ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን የኦሮሚያ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ባሕልና ቱሪዝም ኃላፊ አቶ ጌቱ ወይሳ እንደገለጹት የኢሬቻ በዓል ሥነሥርዓትን በተለያዩ ዝግጅቶች ለማክበር ቅድመ ዝግጅቶች ተጠናቀዋል፡፡

የኢሬቻ በዓልን በማስመልክት ቀደም ሲል የፓናል ውይይትና የሕጻናት የሩጫ ውድድር የተካሄደ ሲሆን፣ በዛሬው ዕለት ደግሞ የአዋቂዎች የሩጫ ውድርና የባሕል ትርዒት እንደሚካሔድ አቶ ጌቱ ገልጸዋል፡፡

አቶ ጌቱ አያይዘውም የዘንድሮውን የኢሬቻ በዓል ለየት የሚያደርገው የበዓሉ መገለጫ የሆነውን የገዳ ሥርዓት በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰሰሱ ቅርነት በሚመዘገብበት ወቅት በመሆኑ ነው፡፡

በየዓመቱ የሚከበረው በዓል የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶችን እየሳበ እንደሆነና የኦሮሞ ባሕልን በማስተዋወቅ ረገድ ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ነው ብለዋል፡፡

የኢሬቻ በዓልን በማስመልከት በትላንትናው ዕለት በፒራሚድ ሆቴል በተካሄደው የፓናል ውይይት ጥናት የኢሬቻ በዓል የኦሮሞን ሕዝብ ባሕላዊ፣ ማሕበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማንንትን የሚገልጽ መሆኑን ተመልክቷል፡፡

በክልሉ የማይዳሰሱ ቅርሶች ባሕልና ቅርስ ጥበቃ ቡድን አስተባባሪ አቶ ስንታየሁ ቶላ የኢሬቻ በዓልን ሳይከለስና ሳይበረዝ ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ የተለያዩ ዝግጅቶች ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

በኢሬቻ በዓል በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሚከበር ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል፡፡