ጋዜጠኛ ጳውሎስ የኮሜሳን የዘገባ ልህቀት ሽልማት አሸነፈ

ኢትዮጵያዊው ጋዜጠኛ ጳውሎስ በለጠ የምስራቅና የደቡብ አፍሪካ አገራት የጋራ ገበያ(ኮሜሳ) የሚያዘጋጀውን የተቀናጀና ብቃት ያለው ዘገባ አቅራቢ ሽልማት ተሸላሚ ሆነ፡፡

ኮሜሳ ጋዜጠኞችን በማወዳደር መሸለም ከጀመረበት እአአ ከ2009 ጀምሮ ጋዜጠኛ ጳውሎስ የኮሜሳን ሽልማት ሲያገኝ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ መሆኑን ኮሜሳ በድረ ገፁ አስነብቧል፡፡

ጋዜጠኛ ጳውሎስ 2000 ዓ.ም ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ የተመረቀ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም በዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል በድረ ገፅ ዋና ክፍል በእንግሊዘኛ ዜና አዘጋጅነት እየሰራ ይገኛል፡፡

በዘንድሮው የኮሜሳ የጋዜጠኞች ውድድር ከዘጠኝ አገራት 30 ፅህፎች ለውድድር ቀርበው የሶስት ጋዜጠኞች ፅሁፎች ተመርጠዋል፡፡ ከጋዜጠኛ ጳውሎስ በተጨማሪ ከቡሩንዲ ሚስተር ሊዮኒዳስ ኒንተረሴ፣ ከዛምቢያ ፍራንሲስ ሉንጉ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ አሸናፊ የሆኑ ፅሁፎች እአአ በ2015 ከጥር እስከ ታህሳስ ድረስ ለህትመትና ለስርጭት የበቁ ናቸው፡፡

የማዳጋስካር ፕሬዚዳንት ሚስተር ሄሪ ራጃናሪማፒያኒና ለተሸላሚዎቹ ሽልማት አበርክተዋል፡፡ በቤተ መንግስትም የእራት ግብዣ አድርገውላቸዋል፡፡

ኮሚሳ በመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ እአአ በ2009 በዚማባቡዌ ባካሄደው 13ኛው ስብሰባ ነበር ጋዜጠኞችን በማወዳደር መሸለም የጀመረው፡፡ ከዛን ጊዜ ጀምሮ በብሮድካስት፣በህትመት መገናኛ ብዙኃን ዘርፍ የቀጣናውን አገራት ትብብር ለማጠናከር የሚረዱ ፅሁፎች፣ ዶክመንተሪዎችና መሰል የሚዲያ ውጤቶችን በማዘጋጀት ያሳተሙና ያሰራጩ ጋዜጠኞች እንዲወዳደሩ ይጋብዛል፡፡

የኮሜሳ ዋና ፀኃፊ ሲንዲሶ ንዌንያ በበኩላቸው ‹‹ መገናኛ ብዙኃን ለህብረተሰቡ የሚጠቅሙ መረጃዎችን በማጠናቀር፣ በማዘጋጀትና በማሰራጨት ትልቅ ሚና አላቸው፡፡ ህብረተሰቡን የሚያሳውቁና የሚያስገነዝቡ መረጃዎችን ከማድረስ በተጨማሪ ለውይይትና ክርክር የሚረዱ የተመረጡ ርዕሶችን በመምረጥና አጀንዳዎችን በመቅረፅ ይሰራሉ›› ብለዋል፡፡

ጋዜጠኛ ጳውሎስ የመገናኛ ብዙኃን ዘርፍን ከተቀላቀለበት ከታህሳስ ወር 2000 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ፎርቹን፣ በካፒታልና በኢትዮጵያ ቢዝነስ ሪቪው ሰርቷል፡፡ በተለያዩ የቢዝነስ፣የጥናትና ምርምር ሥራዎች ላይም ተሳትፏል፡፡