አጀንሲው ከቴምብር ሽያጭና ከአገልግሎት 55 ሚሊየን ብር መሰብሰቡን ገለጸ ፡፡

ፌደራል የሰነዶች ማረጋጫና ምዝገባ ኤጀንሲ ከቴምብር ሽያጭና ከአገልግሎት ክፍያ 55 ሚለየን ብር መሰብሰቡን ገለጸ ፡፡

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን አማረ ከዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ጋር ባደረጉት ቆይታ ባለፉት ሶስት ወራት 86 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅደው 64 በመቶ ለመፈጸም ችሏል ፡፡

እንደዚሁም ለመንግስት 56 ሚሊየን ብር ፈሰስ ለማድረግ ታቅዶ 34 ሚሊየን ብር ፈሰስ መደረጉን ጠቁመዋል ፡፡

ኤጀንሲው በሩብ በጀት ዓመቱ 180 ሺ 913 ጉዳዮችን ለማስተናገድ ያቀደ ሲሆን ፤ከዚህ ውስጥ 154 ሺ 200 ጉዳዮች ማለትም 84 በመቶ በላይ ተከናውኗል ብለዋል ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በተገልጋይ ደረጃ ከ385 ሺ በላይ ተገልጋዮች ለማስተናገድ ታቅዶ 304 ሺ 940 ተገልጋይ ማስተናገዳቸውንም አስታውቀዋል ፡፡

በተለይ የተገልጋይ ቁጥር ያነሰበት ምክንያት አንዱ ኤጀንሲው ከተሰጠው ስልጣን አንጻር ምስክሮችን ያስቀረባቸው የአገልግሎት ዓይነቶች ስላሉ መሆኑን አስረድተዋል ፡፡

ኤጀንሲው የተሳለጡ አገልግሎት ከመስጠት አንጻር አላስፈላጊ የሆኑትን የተገልጋዮች ምስክሮች ከማስቀረት አንጻር የቀነሰበት ሁኔታ ይታያል ነው ያሉት ፡፡

ኤጀንሲው ቃለ ጉባኤ ከማጽደቅ አንጻር በከተማው ያሉ ከ50 በላይ አክስዮን ማህበራት በኤጀንሲው በአካል በመገኘት እንዲፈርሙ የማድረግ አሰራር የነበረ ሲሆን አሁን ይህ መቅረቱን አመልክተዋል ፡፡

ይህም የአክሰዮን ማህበራት ማሻሻያ ቃለ ጉባኤ በሚኖርበት ሰዓት ለማህበሩ አስተዳዳሪዎችና ለጉባኤ አባላት ብቻ እንዲከናወን የተደረገበት አግባብ ስላለ የተገልጋዮች ቁጥር ቢቀንስም አገልግሎቱ እየተሰጠ መሆኑን አብራርተዋል ፡፡

ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ መጠነኛ መቀዛቀዝ ይታይ ነበር ያሉት ምክትል ዋና ስራ አስኪያጁ አሁን ግን የሀገሪቱ ሰላም ወደነበረበት በመመለሱ ወደ ጥሩ መስመር የመግባት ሁኔታ መኖሩን ነው ያስረዱት ፡፡

በቀጣይም በኤጀንሲው በዴሬዳዋ የተከፈተው ጨምሮ በአዲስ አበባ ባሉት 14 ቅርንጫፎቹ የሚታዩ የአሰራር ክፍተቶችን በማስተካከል ለህብረተሰቡ የተሻለ አገልገሎት ለመስጠት እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን አስታውቀዋል ፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት ከ2 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ተገልጋዮችንና ጉዳዮችን በማሰተናገድ 350 ሚሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅደው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን አቶ ሙሉቀን አስታውቀዋል ፡፡