መዳወላቡ ዩኒቨርሲቲ ከ3ሺ በላይ ተማሪዎን ተቀብሎ ማስተማር መጀመሩን አስታወቀ

መዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ከ3ሺ በላይ መደበኛ ተማሪዎች ተቀብሎ ማስተማር መጀመሩን አስታወቀ ፡፡

የዩኒቨርሲቲው የውጭና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ዘውዴ ከዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ በአዲሱ የትምህርት ዘመን 3ሺ170 መደበኛ ተማሪዎች ምዝገባቸውን አጠናቀው ትምህርት ጀምረዋል ፡፡

ተማሪዎች ቀደም ሲል በነበረው አለመረጋጋት ተፈጥሮባቸው የነበረው ሥጋት ወደ የኒቨርሲቲው ከገቡ በኋላ ደስተኞች እንደሆኑና የመማር ማስተማሩ ሂደትም በጥሩ ሁኔታ መቀጠሉን አቶ ተስፋዬ ገልጸዋል፡፡

ለዚሁም ዩኒቨርሲቲው 8 አውቶቡሶችን በማሰማራት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ድረስ ተማሪዎቹን በማጓጓዝ ሊፈጠር የሚችለውን የትራንሰፖርት ችግርም በመፍታት በተያዘላቸው ጊዜ መሰረት ወደ ዩኒቨርሲቲው እዲገቡ እንዳደረገም አስረድተዋል ፡፡

የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የ2009 የትምህርት ዓመትን ሰላማዊ ለማድረግ ከተማሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር መደረጉን ነው የገለጹት ፡፡

ዩኒቨርሲቲው የሰላም ፎረም አቋቁሞ ተማሪዎች በአክራሪነትና ጽንፈኝነት ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን በማስወገድ ለሰላም እንዲቆሙ የሚያደርግ ተግባራት እያከናወነ እንደሆነም አመልክቷል፡፡

አቶ ተስፋዬ አያይዘውም ትምህርት ሚኒስቴር አብዛኞቹ ተማሪዎች በክልላቸው እንዲመደቡ ማድረጉ በተማሪ ቅበላ ጊዜ መዘግየትን ከመቀነሱም በላይ በዩኒቨርሲቲዎች የሚከሰቱ ግጭቶችን ለመቀነስም ጥሩ መፍትሄ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታም የኮማንድ ፖስቱ መቋቋም በየኒቨርሲቲውና በአካባቢው የነበረውን አለማረጋጋት አሁን ሰላማዊ እንዲሆን አድርጓል ነው ያሉት ፡፡

በኦሮሚያ ክልል፣ በባሌ ዞን በሮቤ ከተማ የሚገኘው የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በ1998 ዓመተ ምህረት እንደተመሰረተ ይታወቃል ፡፡