ድርጅቱ ኢትዮጵያ ብቁ ዜጋ ለማፍራት የምታደርገውን ጥረት ይደግፋል

በበጎ አድራጎት ሥራ ላይ የተሰማራው ህፃናት አድን ድርጅት ኢትዮጵያ እአአ በ2020 የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ብቁ ዜጋ ለማፍራት ያስቀመጠችውን ራዕይ ለማሳካት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለፀ፡፡

ድርጅቱ ‹‹የህፃናትን የማንበብና የመፃፍ ክህሎት ለማሳደግ የሚረዱ ስምንት መርሆዎች›› በሚል ያጠናቀረውን ሪፖርት ይፋ ሲያደርግ ለኢትዮጵያ ድጋፉን እንደሚያደርግ አመልክቷል፡፡

ድርጅቱ እአአ ከ2012 እስከ 2015 በ22 አገራት በ35 የማንበብና የመፃፍ ፕሮግራሞች የማንበብና መፃፍ ክህሎትን ለማሳደግ በሚረዱ ተሞክሮዎች ዙሪያ መረጃዎችን በማሰባሰብ ሪፖርቱን ማጠናቀሩን አስታውቋል፡፡ በኢትዮጵያም በአራት ክልሎች ጥናት መካሄዱ ተወስቷል፡፡

ህፃናትን በመንከባከብና በትምህርት ዘርፍ ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለው መሻሻል የሚደነቅ መሆኑን በኢትዮጵያ የህፃናት አድን ድርጅት ዳይሬክተር ሚስተር ጆን ግርሃም ተናግረዋል፡፡

ድርጅቱ አገሪቱ በህፃናት ትምህርት ዙሪያ የነደፈቻቸው ውጤታማ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች እውን እንዲሆኑ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያዲርግ ገልፀዋል፡፡

የዘርፉ ባለሙያዎች በክልሎች፣ በዞን ትምህርት ቤቶች እና በትምህርት ሚኒስቴር በመገኘት ሪፖርቱን ማጠናቀራቸው ተመልክቷል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስትር ተወካይ አቶ እሸቱ ቸሩ ሚኒስቴሩ ውጤታማ፣ፍትሀዊ፣አሳታፊና ጥራቱን የጠበቀ የህፃናት ትምህርትን የማረጋገጥ ራዕይ አሰቀምጦ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህፃናትን ለመንከባከብና ለትምህርት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ከህፃናት አድን ድርጅት ጋር በትብብር እየሰራ እንደሆነም ነው ያስገነዘቡት፡፡

የሪፖርቱ ግኝቶች የህፃናትን የማንበብና መፃፍ ክህሎት ለማሳደግ በቤተሰብ፣በማህበረሰብና የህፃናትን የማንበብና የመፃፍ ክህሎትን ለማሳደግ በተቋቋሙ ማዕከላት ዙሪያ ሚኒስቴሩ የተሻለ ሥራ ለመስራት እንደሚያግዘው አቶ እሸቱ ተናግረዋል፡፡