የእስላማዊ ቅርሶችን ዓይነትና ሥርጭትን የሚዳስስ መጽሐፍ ተመረቀ

ከሰሜን ሸዋ እስከ ደቡብ ወሎ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙትን የእስላማዊ ቅርሶችን በዓይነትና ስርጭት የሚዳስስ መፅሐፍ በዛሬው ዕለት በፌዴራል የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን አዳራሽ ተመረቀ፡፡

በክብር እንግዳነት የተገኙት የባሕልና ቱሪዝም ሚንስትር ዴኤታ ወይዘሮ ታደለች ዳሌቾ እንደገለጹት  የኢትዮጵጵያን ሕዝቦች፣ ብሔሮችና ብሔረሰቦችን ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ሐይማኖትና ባህል ባከበረ መልኩ ቅርሶችን ከትውልድ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባና ይህም ለአገሪቱ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ዕድገት ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የምርምር ማዕከላት ለቅርስ ምርምርና ዶክሜንቴሽን ትኩረት በመስጠት ለቱሪዝም ዘርፉ ዕድገት ይበልጥ እንዲያግዙ ወይዘሮ ታደለች ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

በስድስት ክፍሎች  ተከፈፍሎ  በ124 ገፆች የተዘጋጀውን መጽሐፍ ዶክተር ሐሰን ሰዒድና ሐሰን ሙሐመድ በጋራ ያሳተሙት መሆኑን  በመጽሐፉ ምረቃ ፕሮግራም ላይ ተገልጿል ።

በመጽሐፉ ከ1,300 ዓመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩ ቋሚና የማይንቀሳቀሱ በርካታ እስላማዊ ቅርሶች ታሪኮች በዝርዝር በፎቶግራፉ ተደግፈው ቀርበዋል፡፡

የመጽሃፉ አሳታሚዎች እንደገለጹት መጽሐፉ  ከሰሜን ሸዋ እስከ ደቡብ ወሎ ያሉ እስላማዊ ቅርሶች ላይ ትኩረት ያደረገው የአርጎባ ብሔረሰብ በተጠቀሱት ቦታዎች ላይ እስልምና ኃይማኖት እንዲስፋፋ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደነበረው ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡

የአርጎባ ብሄረሰብ  በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በአፋርና በሐረሪ ክልሎች ይገኛል፡፡ የብሔረሰቡ ቋንቋ የሆነውን አርጎብኛ ቋንቋን በተለይም በአፋር ክልል በአርጎባ ልዩዞን ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት እንደሆነና በአሁን ወቅት በአርጎብኛ  ቋንቋ የሚሠራ የማህበረሰብ ሬዲዮ እንደሚገኝ የአፋር ክልላዊ መንግስት የአርጎባ ልዩ ወረዳ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኑሩ ሑሴን መሐመድ ገልፀዋል፡፡

በዕለቱ በመፅሐፉ ዙሪያ ከተሳታፊዎች፣ የባህልና ታሪክ ምሁራኖች አስተያያት ተሠጥቶ ውይይት የተካሄደ ሲሆን በመጽሐፉ ፀሃፊዎችም ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

ኢትዮጵያ ነገ የሚከፈተውን የተባበሩት መንግሥታት የሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰሱ ቅርሶች ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ እንደምታዘጋጅ ይታወቃል፡፡