በትግራይ ክልል የቱሪዝም ፍሰቱ እየጨመረ መምጣቱን የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ ፡፡
የቢሮው ህዝብ ገንኙነት ባለሙያ አቶ አባዲ ደስታ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት ፤በሩብ በጀት ዓመቱ ብቻ ከ77 ሺ በላይ የአገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች በክልሉ ታሪካዊ ፣ሃይማኖታዊና ጥንታዊ ቅርሶች ጎብኝተዋል ፡፡
በአንዳንድ የአገራችን አከባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው ሁከት ሳቢያ በክልሉ የቱሪስቶች ይቀንሳል የሚል ግምት ቢኖርም ባንጻሩ የቱሪስቶች ፍሰት በ4 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ገልጸዋል ፡፡
የዚሁ ምክንያትም በክልሉ ያለው አስተማማኝ ሰላም ተከትሎ የመሰረተ ልማቶችና ሎጆች መስፋፋት መሆኑን አስረድተዋል ፡፡
እንደዚሁም በክልሉ በዓዲግራትና በመቐለ ከተሞች የተከበረው የመስቀል በዓልና የአሸንዳ በዓል ለቱሪስቶች መጨመር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን አቶ አባዲ አመልክተዋል ፡፡
ከቱሪስቶቹም ውስጥ ከ12ሺ በላይ ከተለያዩ የዓለም አገሮች የመጡ መሆናቸውን ነው የጠቆሙት ፡፡
በአጠቃላይ በሩብ በጀት ዓመቱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከቱሪስቶች ከ480 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል ፡፡
በክልሉ እየተጠናከረ በመጣው የቱሪዝም እንቅስቀሴም ለ65ሺ ሰዎች የስራ ዕድል ይፈጠራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ባለሙያው ጠቁሟል ፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት በክልሉ የተለያዩ የቱሪዝም መስህቦች ከሚገበኙት ከ81ሺ ቱሪስቶች ከ800 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት መታቀዱን አቶ አባዲ ደስታ ገልጸዋል ፡፡