የአክሱም ጽዮን ሃይማኖታዊ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ ፡፡
በየዓመቱ ህዳር 21 ቀን በደመቀ ስነ ስርዓት የሚከበረው የአክሱም ጽዮን በዓል በሰላዊና በአማረ ሁኔታ ለማክበርና ምዕመናን እና ቱሪስቶች በተረጋጋ ሁኔታ እንዲያሳልፉ አራት ኮሚቴዎች ተቋቋመው እየሰሩ መሆናቸውን የቢሮው ህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ አባዲ ደስታ ገልጸዋል፡፡
እነዚህ ኮሚቴዎችም የቅስቀሳና ማስታወቂያ ፣የጽዳት፣የጸጥታ ማስከበርና የእንግዳ ተቀባይ መሆናቸውን ጠቁመዋል ፡፡
በዚሁም መሰረት ወደ ከተመዋ እየገቡ ያሉት ምእመናንና እንግዶች የሚያርፉበት 20 ሰፋፊ ጊዜያዊ መጠለያ ድንኳኖች ያሉ መሆናቸውን ገልጸዋል ፡፡
እንደዚሁም ቀደም ብሎ የከተማው አስተዳደር ህዝቡን በማሳተፍ የጽዳት ዘመቻ በማድረግ ከተመዋ ውብና ማራኪ እንድትሆን መደረጉን አመልክተዋል ፡፡
የጸጥታ ሃይሎችም ወደ ከተማዋ የሚገቡ ምእምናንና እንግዶች ሃይማኖታዊ በዓሉ በተረጋጋ መንፈስ አክብረው ወደየመጡበት እስኪገቡ ድረስ አስፈላጊው ጥበቃ እየተደረገ መሆኑን ነው ያስታወቁት ፡፡
እንደዚሁም ሆቴሎችና አገልግሎት ሰጪ ተቋሞች እንግዶችን በአግባቡ እንዲያስተናግዱ ምክክር መደረጉን አስረድተዋል ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የአክሱም ዩኒቨርሲቲ በቱሪዝም ልማትና በአርኪዮሎጂ ምርምር ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ ስብሰባ አዘጋጅቶ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋ ማካሄዱን ጠቁመዋል ፡፡
ሃይማኖታዊ በዓሉን ለማክበር ከተለያዩ የአገራችን ክፍሎችና ከውጭ አገሮች ወደ ከተማው ከ400ሺ በላይ ህዝብ ይገኛል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ ህብረተሰቡ በተለይም የጸጥታ ሁኔታ በንቃት እንዲጠብቁ ማሳሰባቸውን የዘገበው ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ነው ፡፡