ጣልያን ለወሳኝ ሁነቶች ምዝገባ የ500ሺ ዩሮ ድጋፍ አደረገች

ጣልያን ኢትዮጵያ ለምታከናውነው የወሳኝ ሁነቶች ምዝገባ በተባበሩት መንግስታት የህፃናት እርዳታ (ዩኒሴፍ) በኩል የ500ሺ ዩሮ ድጋፍ አደረገች፡፡

ድጋፉ የወሳኝ ሁነቶች ምዝገባ ኤጄንሲ በኦሮሚያና በደቡብ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች ለሚከናወኑ የልደት፣ ሞት፣ ጋብቻና ፍቺ ወሳኝ ሁነቶች ምዝገባ የሚውል መሆኑን ኤምባሲው ለዋልታ አስታውቋል፡፡

በጣልያን ኤምባሲ በተደረገው የፊርማ ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተገለፀው ወጥና የተደራጀ የወሳኝ ሁነቶች ምዛገባን በጥራትና በፍጥነት ለማካሄድ አገሪቱ የጀመረችውን ጥረት እውን ለማድረግ የላቀ ሚና ይጫወታል፡፡

ህፃናትን ከጥቃት ለመከላከል፣ መብታቸውን ለማስከበርና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በሚደረገው ሂደትም ጉልህ ድርሻ ያበረክታል ተብሏል፡፡

በኢትዮጵያ የጣልያን ኤምባሲ አምባሳደር ጁሴፔ ሚስትሬታ ‹‹የልደት ምዝገባ ለልጆች የመጀመሪያው ዕውቅና የመስጠት እርምጃ ነው›› ብለዋል፡፡

ልጆች መሰረታዊ አገልግሎትን እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታዎችን ከመፍጠርም በላይ ከጥቃትና ጉዳት ለመከላከል ቁርጠኝነትን የማሳያ መንገድ  መሆኑን ነው ያስገነዘቡት ፡፡

ዓለም ዓቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የወሳኝ ሁነቶች ምዝገባ መንግስት መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ለሚቀርፀው ፖሊሲና ለሚነድፋቸው ስትራጂዎችም ትልቅ ሚና እንደሚጫወት አምባሳደሩ አስገንዝበዋል፡፡

የጣልያን የልማት ትብብር ኤጄንሲ የአዲስ አበባ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሚስ ጂኔቭራ ሌቲዚያ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት የቅድሚያ ትኩረት በመስጠት ለሚያቅዳቸውና ለሚተገብራቸው ተግባራት ኤጄንሲው ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

ለወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ የተደረገው ድጋፍ ወቅታዊ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ ሚስ ጂሊያን ሜሎስፕ ናቸው፡፡

ልጆችን ከተለያዩ ጥቃቶች፣ከአድልዎ፣ ከያለአቻ ጋብቻ፣ከጉልበት ብዝበዛ፣ከህገ ወጥ ዝውውር ለመከላከል የሚደረገውን ሂደት በማገዝ ረገድም ጉልህ ድርሻ እንደሚያበረክት ነው ያብራሩት ፡፡