የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን(ኢቢሲ) አዲስ የቦርድ አባላትና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሹመትን አፀደቀ፡፡
ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው ሁለተኛ ዓመት የሥራ ዘመን ስድስተኛ መደበኛ ስብሰባ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረቡትን ዘጠኝ የቦርድ አባላትና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሹመትን አፅድቋል፡፡
በመሆኑም ዶክተር ነገሪ ሌንጮ የኮርፖሬሽኑ የቦርድ ሰብሳቢ፣ አቶ ተፈራ ደርበው፣ ዶክተር ጌታቸው ድንቁ፣ ወይዘሮ ሙፈርያት ካሚል፣ አቶ አፅብሃ አረጋዊ፣ መጋቢ ዘሪሁን ደጉ፣ አቶ እውነቱ ብላታ፣ወይዘሮ ኪሚያ ጁንዲ የቦርድ አባል እንዲሁም አቶ ስዩም መኮንን የቦርዱ አባልና ፀኃፊ ሆነው ተሰይመዋል፡፡
አቶ ስዩም መኮንን የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆነው እንዲሾሙ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበውን ጥያቄም ምክር ቤቱ በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል፡፡
አቶ ስዩም በአማራ ክልል ከዞን አስተዳዳሪነትን ጨምሮ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ማገልገላቸው ተገልፃል፡፡ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ የአማራ ክልል መገናኛ ብዙኃን ኤጄንሲ የምክትል ዳይሬክተርና ዋና ዳይሬክተር በመሆን ሲያለግሉ መቆየታቸውም ተመልክቷል፡፡
በቆይታቸውም የተጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃትና በጥራ በመወጣት ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገባቸው ነው የተጠቀሰው፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪ ፣ከባህር ዳርና ከእንግሊዝ አገር በተለያዩ ዘርፎች ሁለት የሁለተኛ ዲግሪ እንዳላቸው ተመልክቷል፡፡
መንግስት የጀመረውን በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴ ከግብ ለማድረስ የመገናኛ ብዙኃን ዘርፉን ማሻሻል ተገቢ መሆኑ በመድረኩ ተወስቷል፡፡ አዲሱ ሥራ አስፈፃሚ ቀደም ሲል የነበራቸውን ልምድ በመጠቀም ኮርሬሽኑን የተሻለ ደረጃ ላይ ያደርሳሉ የሚል እምነት ተጥሎባቸዋል፡፡
የቦርድ አባላቱና ዋና ሥራ አስፈፃሚው የተጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃት፣በጥራትና በታማኝነት ለመወጣት ቃለ መሀላ ፈፅመዋል፡፡