ጊቤ ሶስት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ልማቶች እንዲከናወኑ አድርጓል

ጊቤ ሶስት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የአካባቢውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማቶች እንዲከናወኑ አስተዋፅዖ ማበርከቱ ተመለከተ፡፡

የፕሮጀክቱ ግንባታ ከኃይል አቅርቦት በተጨማሪ ለቴክኖሎጂ ሽግግርና ለአካባቢው ህብረተሰብ  ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳ ያላቸው ልማቶች በስፋት እንዲከናወኑ አግዟል፡፡

ፕሮጀክቱን ተከትሎ 120 ኪሎ ሜትር መንገድ በመዘርጋት ተራርቀው የነበሩ ቀበሌዎች በመንገድ እንዲገናኙ ተደርጓል፡፡ ይህም 12 ወረዳዎችና ሶስት ዞኖችን ለማገናኘት ያችላል፡፡

ለአካባው ህበረተሰብ አገልግሎት የሚሰጡ ትምህርት ቤት፣ጤና ጣቢያ፣ፖሊስ ጣቢያዎችና ቤተ እምነቶችም መቋቋማቸው ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡

ለወጣቶች ጀልባ በማቅረብ ዓሳ በማጥመድ ሥራ ላይ እንዲሰማሩ መደረጉንም ተቋሙ ይገልፃል፡፡ በግብርና ዘርፍ ለተሰማሩ የአካባቢው ነዋሪዎችም 20 የውሃ ፓምፖች በመትከል ውሃ በቀላሉ በማግኘት የተሻለ የግብርና ልማት የሚያካሂዱበት ዕድል ተመቻቷል፡፡ ለአርሶ አደሮች ለግብርና ምርት የሚያገለግሉ የመስኖ ፕሮጀክቶች ተገንብተዋል።

በደቡብ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ዳውሮ ዞን የሎማ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ገዛኸኝ በቀለ ጊቤ ሶስት ለአካባቢው ህብረተሰብ ትልቅ ገፀ በረከት መሆኑን ይናገራሉ፡፡

የተለያዩ መሰረተ ልማቶች እንዲሟሉ ከማድረጉም በላይ ለአካባቢው ነዋሪዎች ከፍተኛ የሥራ ዕድል መፍጠሩን ይገልፃሉ፡፡ በፕሮጀክቱ ግንባታ ላይ ከተፈጠረው የሥራ ዕድል በተጨማሪ ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው በቀጣይ የራሳቸውን ገቢ የሚያገኙበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

 የአካባቢው ነዋሪ የሆኑት አቶ ለማ በቀለም የአቶ ገዛኸኝን ሀሳብ ይጋራሉ፡፡ በተለይም ‹‹በአካባቢው የተገነባው ትምህርት ቤት ልጆች የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ትልቅ ሚና ተጫውቷል›› ብለዋል፡፡ በግድቡ በሚፈጠረው ትልቅ ሀይቅ ላይ ለቱሪስቶችና ለአካባቢው ህብረተሰብ የጀልባ አገልግሎት የሚሰጡ ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው ወደ ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡

በግቤ ሶስት ፕሮጀክት ከ32 በላይ አገራት የመጡ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡ አጋጣሚው የቴክኖሎጂ ሽግግርና የሥራ ልምድ ለመቅሰም አስችሏል፡፡

በፕሮጀክቱ ግንባታ የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ከዘጠኝ ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን አብዛኛዎቹ የአካባቢው ወጣቶች መሆናቸው በምረቃው ዕለት ተገልጿል፡፡ የአካባቢው ወጣቶችም በፕሮጀክቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ጊቤ ሶስት የሀድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት 1870 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም አለው፡፡ አሁን ያለውን የአገሪቱን የኃይል አቅርቦት በ94 በመቶ እንደሚያሳድገውም ይጠበቃል፡፡