በአዲስ አበባ ከተማ እየተገነቡ ካሉት በዚህ ዓመት 30ሺህ የጋራ መኖሪያቤቶች ለነዋሪዎች እንደሚተላለፉ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አስታወቁ ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ዛሬ በተካሄደው 12ኛ መደበኛ ስብሰባ የ11ኛው መደበኛ ጉባኤ ላይ ከህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ በአዲስ አበባ እየተገነቡ ካሉት 131ሺህ የጋራ መኖሪያቤቶች ውስጥ 30ሺዎቹ ዘንድሮ ለነዋሪዎች ይተላለፋሉ ፡፡
እነዚህ 17 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ወጪ እየተሰሩ የሚገኙት መኖሪያቤቶች የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ በተሻለ ፍጥነት እንዲሄድ ክትትል እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል ፡፡
የኮንስትራክሽን ስራው ከባድ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤በተለይም ጥራት ከማረጋገጥ አንጻር ያለው ከፍተኛ የአመለካከት ችግር ልዩ ትኩረት የሚሰጠው መሆኑን ነው ያስገነዘቡት ፡፡
ችግሩን ለመፍታት ስልጠናና ውይይት እየተደረገ እንደሚገኝም ነው ያመለከቱት ፡፡
መንግስት በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚታየው ዓቅም ማነስ ለመቃለል በዩኒቨርሲቲዎች የ70/30 የትምህርት መርሃ ግብር እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ድረስ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል ፡፡
ይሁንና ከዩኒቨርስቲዎች የሚመረቁ መሃንዲሶችና ባለሙያዎች ያገኙትን ዕውቀት ወደ ክህሎት ለመቀየር ረጅም የተግባር ልምምድ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡
ስለሆነም ችግሩን ለመፍታት የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢኒስቲትዩት ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል ፡፡
የኮንስትራክሽን ዘርፍ ለሙስና በእጅጉ የተጋለጠ በመሆኑ መንግስት ግልጽነትንና ተጠያቂነትን ለማስፈን የተጠናከረ ጥረት መጀመሩን ነው ያስገነዘቡት ፡፡
በተያዘው ዓመት 39 ሺህ የጋራ መኖሪያቤቶች ለነዋሪዎች መተላለፋቸውን ያሰታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤ለነዋሪዎቹ በማስተላለፍ ረገድ የነበረውን መንገላታት ለማስወገድ ስራው በአንድ መስኮት እንዲሰጥ በማድረግ እስከ 9 ወር ይፈጅ የነበረውን በሶስት ወር እንዲያልቅ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል ፡፡
ይህም የቤቶች ልማትን ለተጠቃሚዎች ከማስተላለፍ አኳያ የተሻለ እርካታ ያረጋገጠ ተግባር እንደሆነ ማስገንዘባቸውን የዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘገባ ያመለክታል ፡፡