በአዲስ አበባ ጨምሮ በሀገሪቱ ክልሎች ከሌላው ጊዜ በተለየ ሁኔታ የቀን የአየር ሙቀት መጠኑ መቀነሱን የብሔራዊ ሜቲዎሮሎጂ ኤጄንሲ አስታወቀ
ባለፉት ጥቂት ቀናት በተደረገ የዳሰሳ ትንበያ በደብረብርሃንና በአዲስ አበባ የቀኑ ዝቅተኛ የአየር ሙቀት ከዐ ዲግሪ ሲልሺየስ በታች ወርዶ መታየቱን ኤጀንሲው ገልጿል፡፡
በሀገሪቱ ደጋማ አካባቢዎች ምስራቅና ደቡብ ትግራይ፣ ምስራቅ አማራ፣ መካከለኛው ምስራቅ እና በደቡብ ደጋማ ቦታዎች የቀኑ ዝቅተኛ የአየር ሙቀት ከ5 ሴልሺየስ በታች ወርዶ እንደነበርም ነው ያመለከተው ፡፡
በሀገሪቱ በበጋ ወቅት ዘንድሮ ዝናብ ባለመከሰቱ ቅዝቃዜው እንዲበረታ አድርጎታልም ነው ያለው ፡፡
ኤጀንሲው ከደቡብ ንፍቀ ክበብ የሚነሳው የጸሐይ ጨረር ወደ ኢትዮጵያ የሚደርሰው ረጅም ርቀት ተጉዞ መሆኑ፣ ሲደርስም ጥንካሬ ስለሚያንሰው እና ከሳይቤሪያ ቀዝቃዛ ስፍራ የሚመጣው የአየር ንብረትም ቀዝቃዛ በመሆኑ ለአየር ንብረቱ መለወጥ ምክንያት መሆኑን ነው ያስረዳው፡፡
ይሁንና እየተስተዋለ የሚገኘው ቅዝቃዜ ከጥር አጋማሽ በኋላ እንደሚቀንስ አስታውቋል ፡፡
ለዚሁም ከበልግ ወቅት መጀመር ጋር ተያይዞ የአየር ሁኔታው መስተካከል እንጀሚር ጠቁሟል ፡፡
በአሁኑ ሰዓት በአብዛኞቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች እህል እየተሰበሰበ በመሆኑ ቅዝቃዜው የጎላ ተጽዕኖ እንደማያሳድርም አስገንዝቧል ኤጀንሲው ፡፡
ሆኖም ያልደረሱ እህሎች ላይ በውርጭ ምክንያት ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ብሔራዊ ሜትዮሮሎጂ አስጠንቅቋል፡፡