አገራችን በወባ በሽታ ከመከላከልና ማዳከም አንጻር ትልቅ ለውጥ ካመጡ አገሮች ተርታ ውስጥ መሰለፏን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ ፡፡
ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት በወባ አማካይነት በሚደርሰው ህመም 50 በመቶ እና ሞት ደግሞ ከ60 በመቶ በላይ መቀነሱን በታህሳስ ወር ላይ የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው ሪፖርት እንደሚያሳይ የሚኒስቴሩ የወባ ፕሮግራም አስተባባሪ ወይዘሮ ህይወት ሰለሞን አስታውቀዋል ፡፡
ይህም በዓለም ላይ የወባ ስርጭት ካለባቸው 40 ከመቶ በላይ ቀነሱ ከተባሉ አገሮች ውስጥ የሀገራችን ውጤት የላቀ መሆኑን እንደሚያመለክት ነው የስረዱት ፡፡
በሀገራችን ወባማ ወረዳዎች የበሽታው ክስተቱ ከዚህ በፊት 50 በመቶ የነበረው አሁን ላይ ወደ 0 ነጥብ 5 በመቶ ደረጃ መውረዱን ወይዘሮ ህይወት ጠቁመዋል፡፡
በዚሁም ኢትዮጵያ ባሁኑ ወቅት በወባ መከላከልና ማዳከም ረገድ ትልቅ ለውጥ ካመጡ አገሮች ተርታ ውስጥ መግቧታን ነው የገለጹት ፡፡
በቀጣይም በሚካሄደው የወባ በሽታ የማጥፋት የስትራቴጂ ጠንካራ መከላከል ላይ ያተኮረ ስራ ይሰራል ብለዋል ፡፡
በዚሁም በመጪዎቹ ሳምንታት ወባን ለማስወገድ በተመረጡ 200 ወረዳዎች ላይ ወባን የማጥፋት ስራ ለመተግበር ዝግጅት የሚደረግበት መሆኑን አብራርተዋል ፡፡
ይህና ወባ በሽታ በፊት ከነበረበት የበሽታ ቁጥርና የሞት ክስተት ከመቀነሱ አንጻር በሁሉም የሀገራችን ክፍል በህብረተሰቡ ዘንድ የመዘናጋት ሁኔታ እንደሚታይ አመልክተዋል ፡፡
ከዚህም የተነሳ በሽታው እንደበፊቱ ስለማይከሰት የአልጋ አጎበሮችን በአግባቡ ያለመጠቀም ሁኔታ በስፋት መኖሩን ነው ጨምረው የገለጹት ፡፡
አሁንም በሀገሪቱ ወባ ቀነሰ እንጂ አልጠፋም ያሉት ወይዘሮ ህይወት ፤ወባ ሲከሰት በአጭር ጊዜ ብዙ ጉዳትና ሞት ሊያደርስ የሚችል አስከፊ በሽታ በመሆኑ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል ፡፡