የከተራ በዓል በድምቀት ተከበረ

የከተራ በዓል በመላ ሀገሪቱ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ዛሬ ተከበረ ።

የከተራ እና የጥምቀት በዓል በተለይም በአዲስ አበባ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጽእ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፣ ብጽኣን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ምእመናን፣ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የውጭ ሀገራት አምባሳደሮች እና በርካታ ቱሪስቶች በተገኙበት በሀገር አቀፍ ደረጃ በጃን ሜዳ ተከብሯል ።

የየድብሩ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች፣ ጥንግ ድርብ የለበሱ መዘምራን፣ ልብሰ ተክህኖ የለበሱ ዲያቆናት፣ ቀሳውስት ምእመናንና ምእመናት የተለያዩ መንፈሳዊ ዝማሬዎችን እያቀረቡ አዳራቸውን ታቦታቱ ባረፉበት ጃን ሜዳ አድርገዋል ።

በየስፍራው የሚገኙ የጸጥታና የትራፊክ ፖሊስ አባላት ታቦተ ጽላቶቹ በሰላም ወደየማደሪያ ስፍራዎቻቸው እንደገቡና የተሽከርካሪዎች መጨናነቅ እንደሌለም ከየስፍራው መግለጻቸው ለማወቅ ተችሏል ፡፡

በነገው ዕለትም የጥምቀት በዓል በምእመኑ ዘንድ በድምቀት ይከበራል።

በዓሉ ኢየሱስ ክርስቶስ በመጥምቁ ዮሃንስ እጅ ለመጠመቅ ወደ ባህረ ዮርዳኖስ የወረደበትን ዕለት ለማሰብ የሚከበር መሆኑን ነው የተመለከተው ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ቀኖና መሰረት ቤተ ክርስቲያኒቱ ከምታከብራቸው ዘጠኝ አብይ በዓላት መካከል አንዱ ጥምቀት መሆኑ ይታወቃል  ። 

የእምነቱ ተከታዮች በዓሉን የሚያከብሩትም ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ በ30 አመቱ የማዳን ስራውን በጥምቀት የጀመረበትን ጊዜ ለማስታወስ እንደሆነም ቤተ ክርስቲያኒቱ ትገልፃለች። 

የጥምቀት በዓል በሚከበርበት ጊዜ በዋዜማው ታቦታቱ ከየቤተ ክርስቲያናቱ ወጥተው በወንዝ ዳር ወይም በሰው ሠራሽ የውሃ ግድብ ዳር በዳስ፣ ድንኳን እንደሚያድሩም አቡነ ጎርጎርዮስ በፃፉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ታሪክ መፅሃፍ ላይ ሰፍሮ ይገኛል።

ሌሊትም ቅዳሴ የሚፈፀም ሲሆን፤ ሲነጋ በባህረ ጥምቀቱ ጸሎተ አኩቴት ተደርሶ አራቱም ወንጌላት ከተነበቡ በኋላ ውሃው ተባርኮ ለተሰበሰበው ህዝብ ተረጭቶ ጥምቀት ይፈጸማል-(ኤፍ.ቢ.ሲ)።