የጥምቀት በዓልን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ጥረቶች ተጠናከረው ቀጥለዋል

የጥምቀት በዓልን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የቅርስ ጥበቃ፣ ቤተመጽሐፍትና ቤተመዘክር ቱሪዝም መምሪያ ገለጸ፡፡

የመምሪያው ኃላፊ መምህር ሰለሞን ቶልቻ ከዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት ካሳፍነው ታሕሳስ ጀምሮ የመረጃ ማሳባሰቡ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል።

የጥምቀት በዓል ከኃይማኖታዊ ፋይዳው ባለፈ ማህበረሰባዊና ባሕላዊ ጥቅሙ በብዙ መልኩ ይገለፃል።

በመሆኑም በዓለም የቅርስ መዝገብ እንዲሰፍር የባህልና ቱሪዝም ሚንስትር፣ የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣንና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ጉዳዩን ትኩረት ሰጥተውት እየሰሩ ነው ብለዋል ኃላፊው፡፡

በዓሉን በየኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስት ለማስመዝገብ የሚያስችሉ ሰነዶች ተሰናድተው ዩኔስኮ ይላካሉ።

በዚህም መሰረት ባለሞያዎችን ወደ ጎንደር፣ ላሊበላ፣ አክሱም እንዲሁም አዲስ አበባ በማሰማራት ክብረ በዓሉን አስመልክቶ መረጃዎች በፎቶግራፍ፣ በጽሑፍ፣ በድምጽና በምስል እየተሰባሰቡ ነው፡፡

የጥምቀት በዓልን  በ2010 ዓ.ም. በደቡብ አፍሪካ በሚደረገው የዩኔስኮ ጉባዔ ላይ በማይዳሰሱ ቅርስነት ለማስመዝገብ እንደታቀደ መምህር ሰለሞን ገልጸዋል፡፡

መምህር ሰለሞን አክለው እንደገለጹት በምዝገባው ሂደት ላይ የሕዝቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ መኖር ወሳኝ በመሆኑ፤ ሰዎች በፊርማቸው ያረጋግጣሉ፤ በቤተክህነት ዙሪያ ያሉ ተቋማት፣ ምዕመናኑ ራሱ ድጋፉን በፊርማ ማረጋገጥ አለበት።

እነዚህ ወሳኝ መስፈርቱን ለማሟላት ወሳኝ ጉዳዮች መሆናቸውም ተመልክቷል፡፡

በተጨማሪም ሕብረተሰቡ እንግዳ ተቀባይነትቱን፣ ሰላም ወዳድነቱን ማስቀጠል አለበት፡፡

በተለይም ወጣቱ ባሕሉንና ኃይማኖቱን በማክበር ወደ ቀጣይ ትውልድ ሳይበረዝ ለማሸጋገር የሚደረገውን ጥረት ማገዝ ይገባዋል ብለዋል፡፡

የገዳ፣ የፍቼ ጨምበላላና የመስቀል በዓላት የማይዳሰሱ የዓለም ቅርሶች ሆነው መመዝገባቸውን  ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል፡፡