በንዌር ዞን እየተገነባ ያለው የመለስ ዜናዊ ሆስፒታል መጓተቱ ተመለከተ

በጋምቤላ ክልል እየተገነቡ ካሉት ሶስት የመለስ ዜናዊ  ሆስፒታሎች ውስጥ የንዌር ዞኑ መጓተቱን የክልሉ ጤና ቢሮ ገለጸ ፡፡

የታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ መታሰቢያነት  ከ2005 ዓመተ ምህረት አንስቶ በ80 ሚሊየን ብር መነሻ ካፒታል በክልሉ በኝንኛንግ፣በኩሚና በፕኝውዶ ከተሞች ሲገነቡ መቆየታቸው ይታወቃል ፡፡

ከነዚህም ውስጥ በኝንኛንግ ከተማ እየተገነባ ያለው ዞናል ሆስፒታል እስካሁን ግንባታው 75 በመቶ ብቻ መጠናቀቁን የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኡማን አመሉ አረጋግጠዋል፡፡

የግንባታው መጓተት ምክንያትም ኮንትራክተሩ ስራውን አቋርጦ በመጥፋቱ መሆኑን ኃላፊው አስታውቀዋል ፡፡

አሁን ግን ክልሉ እንደገና ባወጣው ጫረታ መሰረት ከአንድ ሳምንት በፊት አንድ ኮንትራክተር በማሸነፉ ስራው መቀጠሉን ገልጸዋል ፡፡

ይኸው ኮንትራክተርም ግንባታው በአራት ወራት ውስጥ እንደሚያጠናቅቅ ቃል መግባቱን  ነው ያመለከቱት ፡፡

በአኝወሃ ዞን የሚገኘው ፕኙውዶ ሆስፒታልና በማጃን ዞን የተገነባው ኩሚ ሆስፒታል ባለፈው በጀት ዓመት ተጠናቀው በነሐሴ ወር 2008 ዓመተ ምህረት መመረቃቸውን ገልጸዋል ፡፡

ይሁንና የኩሚ ዞናል ሆስፒታል በሰው ኃይልና በቁሳቁስ በሚገባ ባለመደራጀቱ ምክንያት በመጠኑም ቢሆን ስራው እንዲጀምር መገደዱን ነው ያመለከቱት ፡፡

ይህም ስራውን በአግባቡ ለማካሄድ የስው ኃይልና የቁሳቁስ ለሟሟላት ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል ፡፡

በአኝዋሃ ዞን የሚገኘው የፕኝውዶ ሆስፒታል ግን ስራው በአግባቡ ለህብረተሰቡ እየሰጠ መሆኑን ዶክተር ኡማን አስታውቀዋል ፡፡

በክልሉ ያሉት መለስ ዜናዊ መታሰቢያ ሆስፒታሎች በየዞኑ ለሚገኙት ነዋሪዎች በሙሉ የተሻለ የጤና አገልግሎት ይሰጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቁ ኃላፊው አስረድተዋል ፡፡

የዞኑ ህዝብ የተሻ የጤና አገልግሎት ለማግኘት ወደ ጋምቤላ ከተማና ወደ ደቡብ ክልል ቴፒ ከተማ እንደሚጓዙ ለማወቅ መቻሉን ዋልታ ዘግቧል ፡፡