ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ድርቅ ለመቋቋም የ948 ሚሊየን ዶላር እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ፡፡
ኮሚሽኑ ከሕዳር 7/2009 ጀምሮ በመላው ሀገሪቱ 23 ቡድኖችን በ246 ወረዳዎች በማሰማራት ባከናወነው የዳሰሳ ጥናት 5.6 ሚሊየን ሕዝቦች ለድርቅ መጋለጣቸውንና ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው መለየቱን ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ገልጸዋል፡፡
በመጀመሪያ ዙር ድጋፍ የሚውል የፌደራል መንግስትና ክልሎች በጋራ 75 ሚሊየን ዶላር ወጪ በማድረግ ድጋፉ ለተረጂዎች ምግብ፣ ውሃ፣ መድሐኒትና የእንስሳት መኖን ለመግዛትና ለማከፋፈል እየዋለ እንደሆነ ታውቋል፡፡
ከጠቅላላው የድርቅ ተጋለጭ ቁጥር አንጻር በኦሮሚያ ክልል 36 በመቶ፣ በሶማሌ 29 በመቶ እንዲሁም በአማራ 11 በመቶ ያህል በዋናነት በአርብቶ አደር አካባቢዎች እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ድቁን ለመቋቋምም ከሚያስፈልገው 198 ሚሊየን ብር ያህሉ ለትምህርት ቤት ምገባ እንዲሁም 118 ሚሊየን ብር ደግሞ ለእንስሳትና ዓሳ መድሐኒትና መኖ አቅርቦት ይውላል፡፡
በድርቁ ምክንያት በተወሰኑ አካባቢዎች ላይ እንስሳትን እየገደለ ቢሆንም ጉዳቱ እንዳይከፋ ለማድረግ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን አስገንዝበዋል። በድርቁ ፈጽሞ ሰዎች ለሞት እንደማይዳረጉ ግን እምነታቸው እንደሆነ ኮሚሽነሩ አክለው ገለጸዋል፡፡
እንደ አቶ ምትኩ ማብራሪያ በተለይም ለእንስሳት በቂ መኖ ለማቅረብ አስቸጋሪ በመሆኑ አርብቶ አደሮች እንስሳቱን ወደ ገበያ በማውጣት የሚሸጡበትን ሁኔታዎች ለማመቻቸት ከእንስሳትና ዓሣ ሐብት ልማት ሚንስትር ጋር እየተሰራ ነው፡፡
ቀደም ሲል በተደረገው የመኸር ጥናት ለድርቅ ተጋላጭ የሆኑት ዜጎች ብዛት ከ10.2 ሚሊየን ወደ 9.7 ሚሊየን አሁን ላይ ደግሞ ወደ 5.6 ሚሊየን መቀነስ መቻሉን አቶ ምትኩ ጠቅሰዋል፡፡
መንግስት እስካሁን ድረስ 16.5 ቢሊየን ብር በመመደብ ለኤልንኖ ድርቅ ለተጋለጡ ዜጎችን የምግብና ምግብ ነክ፣ ጤና፣ ትምህርትና ውሃ ድጋፎችን በማቅረብ በሰዎችና በእንስሳት ላይ ሊፈጠር የሚችለውን ችግር ማቃለል እንደተቻለም ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል፡፡