ድርቅን በዘላቂነት መቋቋም የሚችል ዓቅም የመፍጠር ጥረቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል -መንግስት

በመላ አገሪቱ ለዘለቄታው ድርቅን መቋቋም የሚችል ዓቅም ለመፍጠር እየተካሄደ ያለው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን የፌደራል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት

አስታወቀ ።

ጽሕፈትቤቱ ባወጣው ሳምንታዊ መግለጫ እንደገለጸው ፤በአሁኑ ወቅት ከ22 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በተፋሰስ ልማት ስራ ላይ ተሰማርቶ እየሰራ ይገኛል።

የኢፌዴሪ መንግስት ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ያለውን ችግር በጊዜያዊነት ለመፍታት በዋናነት በራሱ አቅም የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያለው ፡፡

ዓለም አቀፍ ተቋማትና ወዳጅ ሀገራትም ችግሩን ለመቋቋም በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ማስተባበሩን ይቀጥላል፡፡ 

ድርቁ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ያለው ማህበረሰብ እና መላው ህዝባችን እያደረጉት ያለውን ርብርብ እንዲሁም ድርቅን በዘላቂነት ለመቋቋም በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚደረገው የልማት ስራዎች ርብርብ እያሳዩ ያሉትን የነቃ ተሳትፎ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስቧል ።

ዘንድሮ  በአንዳንድ ቆላማ የአርብቶ አደር አካባቢዎች ያጋጠመው ድርቅ  የሚያስከትለውን አደጋ ለመቋቋምም የኢፌዴሪ መንግሥት፣ የክልል መንግሥታት፣ የየአካባቢው ማህበረሰብ እና መላ ህዝቡ የጋራ ርብርብ እያደረጉ ይገኛሉ ብሏል ።

የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት በጋራ ለ 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ህዝብ ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ እርዳታዎችን እያቀረቡ እንደሚገኙም ጠቅሷል ።

የመጠጥ ውሃ በቦቴ በማመላለስ፣ የእንስሳት መኖ አቅርቦት እና የህክምና አገልግሎትም ለድርቁ ተጠቂዎች እየተሰጠ እንደሚገኝም እንዲሁ ።

በድርቅ በተጠቁት አካባቢዎች የሚኖሩ የአርብቶ አደር ልጆች ከቀያቸው ሳይርቁ ትምህርታቸውን መቀጠል እንዲችሉም ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጿል ፡፡ በዚህም የፌዴራል መንግሥት ከመደበው ሀብት በተጨማሪ ክልሎች የየራሳቸውን በጀት በመጨመር የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም በመጀመሩ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ማድረግ መቻሉንም አስታውቋል ።

ድርቅን በመቋቋም ረገድ ባለፈው ዓመት የተገኙ በጎ ተሞክሮዎችን  በማስፋትም የድርቅን ተጽዕኖና ዘላቂ ጉዳት የመቋቋም አቅምን ለማጎልበት እየተሰራ እንዳለም አስረድቷል ። ለአብነትም መስኖ ባለባቸው አካባቢዎች በፍጥነት የሚደርሱ የእንስሳት መኖዎችን የማልማት ሥራ እየተካሄደ መሆኑን ነው የጠቆመው ። 

ዓምና የኢፌዴሪ መንግሥት ችግሩን በወሳኝነት በራስ አቅም ለመፍታት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በተደረገ ርብርብ በድርቁ አንዳችም ዓይነት ሰብዓዊ ቀውስ እና ጉዳት ከመድረሱ በፊት አደጋውን መቋቋም መቻሉን አንስቷል ፡፡

ይህ ድርቅን የመቋቋም ተግባራችንን ከዚያ በፊት ከነበረው ተመሳሳይ እንቅስቃሴዎቻችን የተለየ ያደረገውም ይኸው በወሳኝነት በራሳችን ሀገራዊ አቅም አደጋውን መቋቋም መቻላችን ነበር ነው ያለው ።

በዓለማችን በተከሰተው የተፈጥሮ አየር መዛባት ሳቢያ ባለፈው ዓመት በ50 ዓመት ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ከባድ ድርቅ አጋጥሞን እንደነበር አይዘነጋም።