በአዲስ አበባ ከተማ በዘንድሮ የበጀት ዓመት 123ሺ ሰዎችን በልማታዊ የሴፊቲኔት መርሃ ግብር ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተካሄዱ መሆኑን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የማህበራዊ ጥበቃ ፈንድና ልማታዊ ሴፍቲኔት ኤጀንሲ አስታወቀ ።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ተሻለ ዮና ለዋልታ እንደገለጹት መንግሥት የያዘውን የድህነት ቅነሳ ስትራቴጂ ተግባራዊ ለማድረግ በዘንድሮ የበጀት ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ በ 35 ወረዳዎች የሚገኙ 123ሺ ነዋሪዎችን የልማታዊ ሴፍቲኔት መርሃ ግብር ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዷል ።
በዘንድሮ የበጀት ዓመት በሴፍቲኔት መርሃ ግብሩ ተጠቃሚ ከሚሆኑት የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል 100 ሺ የሚሆኑ በማህበረሰብ አቀፍ ሥራዎች የሚሳተፉ ናቸው ያሉት አቶ ተሻለ 23 ሺ የሚሆኑት በመርሃ ግብሩ የቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል ።
በአሁኑ ወቅት የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚዎችን ለመለየት ኮሚቴዎች ተቋቁመው ከየካቲት 6 ጀምሮ በአዲስ አበበ ከተማ 35 የሚሆኑ ወረዳዎች የቤት ለቤት ምዝገባ መጀመሩን የሚናገሩት አቶ ተሻለ ምዝገባው እስከ የካቲት 20 እንደሚቀጥል ጠቁመዋል ።
በበጀት ዓመቱ የልማታዊ ሴፍቲኔት መርሃ ግብሩን ለማስፈጸም ከመንግሥትና ከዓለም ባንክ በተገኘ ብድር በአጠቃላይ 647 ሚሊዮን ብር መመደቡን ያስረዱት አቶ ተሻለ ከበጀቱ ውስጥ 428 ሚሊዮን ብር የሚሆነው ለማህበረሰብ አቀፍ ሥራዎች ቀሪው 219 ሚሊዮን ብር ለቀጥታ ድጋፍ ይውላል ብለዋል ።
እንደ አቶ ተሻለ ገለጻ በሴፍቲኔት መርሃ ግብሩ ተጠቃሚ የሆኑት ነዋሪዎች የቀን ገቢያቸው 18ብርና ከዚያ በታች የሆኑና ከድህነት ወለል በታች እንደሚገኙ ተረጋግጦ በመርሃ ግብሩ እንዲካተቱ ይደረጋል ።
በልማታዊ ሴፍቲኔት መርሃ ግብሩ ትግበራ መሥራት የሚችሉ ሥራ አጥ ወጣቶች በማህበረሰብ አቀፍ የተለያዩ ሥራዎች ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ በዘላቂነት ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ ድጋፍ እንደሚሠጣቸው አቶ ተሻለ ተናግረዋል ።
በአዲስ አበባ ከተማ ጧሪና ቀባሪ ያጡ አረጋውያን ፣ የአዕምሮ ህመምተኞች፣ ጎዳና ተዳዳሪዎች፣ለምኖ አዳሪዎችና ሴተኛ አዳሪዎች በመርሃ ግብሩ የቀጥታ የምግብ ዋስትና ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል ።
በአገሪቱ በሁለት ምዕራፎች ለአሥር ዓመት ተግባራዊ በሚደረገው የከተሞች ልማታዊ የሴፍቲኔት መርሃ ግብር በአጠቃላይ በ 972 ከተሞች 4ነጥብ7 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዷል ።