የኢትዮጵያ ባለውለታ የነበሩት ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት አረፉ

የኢትዮጵያ ባለውለታ የነበሩት ፕሮፈሰር  ሪቻርድ ፓንክረስት  በ90  ዓመታቸው  ማረፋቸውን  የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታወቀ ።   

ፕሮፌሰር ፓንክረስት የኢትዮጵያ ትልቅ  ባለውለታ ከሆኑት ሙሁራኖች መካከል የሚመደቡ ሲሆን  በህይወት ዘመናቸው የኢትዮጵያን  ባህል ፣ ታሪክ፣  ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና ማህበራዊ ጉዳዮች  በማጥናት የቀረው ዓለም  እንዲያውቀው የሚያስችሉ  በርካታ ሥራዎችን ሠርተዋል ።   

የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ለዋኢማ በላከው መግለጫ  ፕሮፈሰር ሪቻርድ ፓንክረስት  ከዚህ ዓለም በሞት በመለየታቸው የተሰማውን  ጥልቅ ሃዘን ገልጿል ።

የኢትዮጵያ ታሪክ ታላቅ ምሁር የሆኑት ፕሮፈሰር ፓንክረስት በተለይ ከእናታቸው ሲልቪያ ፓንክረስት ጋር በመሆን  ኢትዮጵያ በጣሊያን በተወረረችበት ወቅት  ኢትዮጵያውያን የፀረ -ጣሊያን  ትግልን  በመደገፍ  ትልቅ አስተዋጽኦ  ያበረከቱ  ሲሆን  እኤአ በ1956  ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ  በኢትዮጵያ ታሪክ ፣ ባህልና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ  የተለያዩ  ጥናቶችን በማካሄድ ከ 20 በላይ መፅሓፍትን  አሳትመዋል ።

ፕሮፌሰር ፓንክረስት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ጥናት ተቋምን  በማቋቋም ትልቅ ሚና ከመጫወታቸውም  በላይ የኢትዮጵያ  ወዳጆች ማህበርን እንቅስቃሴ በመምራትም ይታወቃሉ ።        

የአክሱም ሐውልት ከጣሊያን ወደ አገሩ ተመልሶ እንዲመጣ  በማድረግ በኩልም  ፕሮፌሰር ፓንክረስት እልህ አስጨራሽ  ትግል ያደረጉ ሲሆን   በቅርቡም ከፕሬዚደንት  ላደረጉት  አስተዋጽአ  የእውቅና ሽልማት  ተሠጥቷቸዋል ። በኢትዮጵያ  የጥናት  ሥራቸውም ከእንግሊዝ መንግሥት ሽልማት አግኝተዋል ።  

የኢፌዴሪ የውጭ  ጉዳይ ሚንስትር ዶክተር ወርቅነህ  ገበየሁ ታላቁ  ፕሮፌሰር በሞት በመለየታቸው የተሰማቸወን ጥልቅ ሃዘን  ለባለቤታቸው  ሪታ  ፓንክረስት ለልጆቻቸው ሄለንና አሉላ እንዲሁም ለመላ ቤተሰቦቻቸው  አስተላልፈዋል ።