የሞጆ-ሓዋሳ የፈጣን መንገድ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ 12 በመቶ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን አስታወቀ ።
የቻይና ሬል ዋይ ሰቨንዝ ግሩፕ የሞጆ -አዋሳ የፈጣን መንገድ ፕሮጀክትን በ3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ለማከናወን ከሁለት ዓመት በፊት መስማማቱ ይታወሳል ።
የመንገድ ፕሮጀክቱን ወጪ የሚሸፈነውም ከኢትዮጵያ መንግሥት በተመደበ በጀትና ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ ብድር ነው ።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ለዋልታ እንደገለጹት የሞጆ -መቂ የፈጣን መንገድ ፕሮጀክትም የሞጆ -ሐዋሳ የፈጣን መንገድ አካል መሆኑንና የሞጆ -ሃዋሳ ፈጣን መንገድ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ በ2011 ዓም ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል ።
እስካሁን ድረስ የሞጆ-ሐዋሳ ፈጣን መንገድ የግንባታ ሥራ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ሳምሶን የመንገድ ግንባታ ሥራ አፈጻጻም ፕሮጀክቱ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ እንደሚጠናቀቅ ያመላክታል ብለዋል ።
የመንገድ ፕሮጀክቱን የጥራት ደረጃውን ለመጠበቅም ልምድ ያላቸው አማካሪዎችና ተቆጣጣሪዎች ክትትል እያደረጉ መሆኑን አቶ ሳምሶን አስረድተዋል ።
የፈጣን መንገድ ፕሮጀክቱ የተቀሩት ሦስር ምዕራፎች መቂ-ዝዋይ ፣ዝዋይ-አርሲ ነገሌና አርሲ ነጌሌ-ሃዋሳ የመንገድ ግንባታዎች መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ሳምሶን በአጠቃላይ 145 ኪሎሜትር የሚረዝመው መንገድ ከአገር ውስጥና ከውጭ በተገኘ ገንዘብ ይገነባሉ ብለዋል ።
የዓለም ባንክና የቻይና ኤግዚም ባንክ የፈጣን መንገዱ በገንዘብ በመደገፍ በኩል ዋነኛ የገንዘብ ተቋማት ናቸው ።
( ትርጉም : በሰለሞን ተስፋዬ)