የኢትዮጵያ አየር መንገድ 184 የአቪዬሽን ባለሙያዎችን አስመረቀ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አቅሙን ለማሳደግና አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል 184 የአቪዬሽን ባለሙያዎችን አስመረቀ፡፡

ከተመራቂዎቹ መካከል 90 ከበረራ አስተናጋጅና ከምግብ ዝግጅት፣84 ከአውሮፕላን ቴክኒሺያን ማሰልጠኛ ቀሪዎቹ ደግሞ ከቴክኒሺያንና ጥገናና ትምህርት ቤት ሰልጥነው የተመረቁ መሆኑን ጋርድያን ዘግቧል፡፡

የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም አየር መንገዱ አገልግሎት አሰጣጡን ይበልጥ ለማሻሻልና ለማቀላጠፍ ለስልጠና ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናረዋል፡፡

በመሆኑም አየር መንገዱ ወጣት ኢትዮጵያውያንና አፍሪካውያን የአቪዬሽን ባለሙያዎችን በጥራትና በብዛት በማፍራት የአፍሪካን አየር መንገድ ውጤታማ ለማድረግ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

‹‹የአቪዬሽን አካዳሚው ዓለም ዓቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ውጤታማ ሥራ እየሰራ ነው›› ያሉት አቶ ተወልደ የአየር መንገዱን እአአ 2025 ዕቅድ ለማሳካት የሚያስችል አቅም እየፈጠረ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የአካዳሚውን አቅም በማሳደግ የሰልጣኖች የቅበላ አቅሙን አሁን ከደረሰበት አንድ ሺ በ2025 አራት ሺ ለማድረስ ይሰራል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አቪዬሽን አካዳሚ በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን፣ በአሜሪካ ፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር፣በአውሮፓ አቪዬሽን ደህንነት ኤጄንሲ ብቃቱ ተረጋግጦ ዕውቅና የተሰጠው ተቋም ነው፡፡

አየር መንገዱ በአውሮፕላን አብራሪነት፣ በአውሮፕላን ጥገናና ቴክኒሽያንነት፣ በበረራ አስተናጋጅነት፣ በምግብ ዝግጅት፣ በማርኬቲንግና በተለያዩ ዘርፎች ስልጠናዎችን በመስጠት ባለሙያዎችን እያፈራ ይገኛል፡፡