የኢትዮ -ሱዳን የህዝብ ትራንስፖርት እሁድ ይጀመራል

በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የሚደረገው የኢትዮ -ሱዳን የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት እሁድ እንደሚጀመር ተገለፀ፡፡

የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሁለቱን አገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር የላቀ ሚና እንደሚጫወት በፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን የህዝብ ትራንስፖርት ብቃት ማረጋገጫ ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ በላቸው ለዋልታ ተናረግዋል፡፡

የአገልግሎቱ መጀመር የሁለቱ አገራት ዜጎች በነፃነት የሚንቀሳቀሱበትን መልካም አጋጣሚ ከመፍጠሩም በላይ የሁለትዮሽ ትስስሩን በማሳለጥ በአገራቱ መካከል ንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ቱሪዝምና መሰረተ ልማትን ለማስፋፋት ይረዳል ብለዋል-አቶ ተስፋዬ፡፡

የትራንስፖርት አገልግሎቱን ለመጀመር ባለፉት ስምንት ዓመታት በሁለቱ አገራት መካከል የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በስፋት ሲከናወኑ መቆየታቸውን አቶ ተስፋዬ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮ- ሱዳን የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ጥምር ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ወጋየሁ አራጋው በበኩላቸው የሙከራ አገልግሎቱ እሁድ እንደሚጀመር ጠቁመው በተመሳሳይ ቀንና ሠዓት ከሁለቱም አገራት የህዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪዎቹ ተሳፋሪዎችን ጭነው በመነሳት መተማ ላይ እንደሚገናኙ ተናግረዋል፡፡ መተማ ላይ የሙከራ አገልግለቱ ማብሰሪያ ፕሮግራም ተካሂዶ ተሸከርካሪዎቹ ጉዞ እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል፡፡

ጥምር ኮሚቴው ስታዲየም አካባቢ የሓ ሲቲ ሴንተር ህንፃ ላይ ቢሮ በመክፈት ለተሳፋሪዎች ትኬት መቁረጥ መጀመሩን ሊቀመንበሩ ተናግረው የጉዞ ተመኑም 60 ዶላር መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡  

አቶ ወጋየሁ እንዳሉት ከአዲስ አበባ ካርቱም እንዲሁም ከካርቱም አዲስ አበባ የሚደረገው ጉዞ ሁለት ቀን ይፈጃል፡፡ አሁን በሙከራ ደረጃ የሚጀመረው አገልግሎት ለሁለት ወር ይቆያል፡፡ የጉዞ አገልግሎቱ በሳምንት ሁለት ቀን ሰኞና ሀሙስ የሚደረግ ሲሆን ለአሽከርካሪዎችና ረዳቶች ተገቢው ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

በኢትዮ-ሱዳን የህዝብ ትራንስፖርት ጎልደን፣ ዓባይ፣ ሠላምና ኢትዮ ባስ አገልግሎቱን እንደሚሰጡ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከአዲስ አበባ ወደ ሱዳን ለሚደረገው ጉዞ በተደረገው የዕጣ ድልድል ዓባይ ባስ የመጀመሪያው ተጓዥ ሆኗል፡፡ በአገልግሎቱ የሚካፈሉት አራቱ የህዝብ ትራንስፖርት ድርጅቶች  አገልግሎቱን ለመስጠት አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን ኃላፊዎቹ ለዋልታ ተናረግዋል፡፡